ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

በትግራይ መቐለ ከተማ ተቋርጦ የነበረው የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት መመለስን ተከትሎ ነዋሪዎችን አነጋግረናል።

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
በትግራይ መቐለ ከተማ ተቋርጦ የነበረው የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት መመለስን ተከትሎ ነዋሪዎችን አነጋግረናል።

ነዋሪዎቹ " ጭልምልም ብሎብን ነበር። አሁን ከወዳጅ ዘመዶቻችን ጋር ስለተገናኘን ደስ ብሎናል " ብለዋል።

" አሁን በከተማዋ የተሻለ መረጋጋት አለ ፤ አልፎ አልፎ ከሩቅ የተኩስ ድምጽ ይሰማል ተኩሱ የትግራይ ሰላም ኃይሎች ከበረሃ ወደ ከተማ ሲገቡ ስለሚተኩሱ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

ትናንት ከረፋድ አንስቶ እግረኛ የኢትዮጵያ መከላከለያ ሰራዊት ሲገባ እንደነበር እና ከሰዓት ከ11:0ዐ በኃላ በመኪና በርካታ ኃይል ገብቶ ማደሩን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የንግድ ሱቆች፣ ቁርስ ቤቶች፣ ሆቴሎች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪዎች ወደ መደበኛ ስራቸው ሙሉ በሙሉ ገብተዋል ባይባልም ተዘግተው የነበሩ አንዳንድ የስራ ቦታዎች ዛሬ ሲከፈቱ እንዳዩ ገልጸዋል።

የፀጥታ ሁኔታው አሁን ባለበት ከቀጠለ መደበኛ እንቅስቃሴ ቶሎ ይጀምራል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

" አሁንም ጭንቀቶች አሉ ማህበረሰቡ እየተደራጀ አካባቢውን እየጠበቀ ነው። መከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማዋ በመግባቱ ተስፋ ሰጥቶናል " ብለዋል።

" ዳግም ግጭቱ ሲያገረሽ ' መከላከያ ሰራዊቶች ይመጡባችኋል ' እየተባለ ሰው ንብረቱን ወደ መኖሪያ ቤት እንዲያሸሽ ሲደረግ ነበር " ያሉት ነዋሪዎቹ  ነገር ግን መከላከያ ሰራዊቱ መቐለ ሲገባ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ተናግረዋል።

ዝርፊያ የነበረው ህወሓት ወጥቶ መከላከያ እስኪገባ በተፈጠረው ክፍተት እንደነበር ጠቁመዋል።

ሀገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ሰላም ኃይል ጋር በመሆን ከተማውን የመጠበቅና ህዝቡን የማረጋጋት ስራ እየሰራ እንዳለ አመልክተዋል።

ሀገር መከላከያ እና የትግራይ ሰላም ኃይል መቐለ ከመግባታቸው በፊት (ከትናንት በስቲያ ምሽት) በከተማው የነበሩ ታጣቂዎች ከፍተኛ ስርቆት ሲፈጽሙ ነበር ብለዋል ነዋሪዎቹ።

የመንግስት ተቋማት እና የግለሰብ ንብረቶች መዘረፋቸውን አመልክተዋል።

" በተለይ የመንግስት ተቋማት በሆኑት እንደ ፍርድ ቤቶች ባሉት ላይ ዘረፋውን ያስጀመሩት የህወሓት ታጣቂዎች ናቸው። ኮምፒውተሮች ተወስደዋል " ሲሉ ተናግረዋል።

" ታጣቂዎቹ ዘርፈው ሲወስዱ የተረፈውን ሌሎች ሌቦች ናቸው የሰረቁት። ታጣቂዎቹ ዘረፋውን ያቆሙትም ተኩስ ሲጀመርባቸው ነው " ሲሉ አክለዋል።

የህወሓት ኃይሎች በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች መሳሪያ ከነ ጥይቱ ትተው በመሄዳቸው ትንንሽ ታዳጊዎች ሳይቀሩ ከዛ እየወሰዱ ታጥቀው መታየታቸውን ድንጋጤን የፈጠረ እንደነበር ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪዎች አመልክተዋል።

ነዋሪዎቹ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ መቐለ ከተማ እየመጡ መሆኑ ሲሰማ ህወሓት ያለውን ኃይል ይዞ ወደ አክሱም ማጓጓዙን ገልጸዋል።

" በመቐለ ከተማ ወጣት የሚባል ሁ የህወሓትን አፈሳ ፈርቶ ከቤቱ ወደ ውጭ አይወጣም ነበር " ያሉት ነዋሪዎቹ " በቀን ቢያንስ 100 ወጣት አፍሰው ሲወስዱ ስንመለከት ነበር ፤ አሁን ላይ ግን በተፈጠረው ነገር ደስተኛ ነው ወጣቱ " ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ ሰላም ኃይል ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠሩ በርካታ ወጣቶችና ነዋሪዎች አቀባበል ሲያደርጉ ደስታቸውንም ሲገልጹ እንደነበር አስረድተዋል።

ነዋሪዎቹ " አሁን ቢያንስ እፎይታ አግኝተናል " ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መስከረም 24 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች