ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

‎"... በየትኛውም መመዘኛ የወጣቶቹ ግድያ ትክክል አይደለም ፤ እውነት ህግ ካለ ርሸና የፈጸሙ አካላት ሊጠየቁ ይገባል " - ነዋሪዎች

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
‎"... በየትኛውም መመዘኛ የወጣቶቹ ግድያ ትክክል አይደለም ፤ እውነት ህግ ካለ ርሸና የፈጸሙ አካላት ሊጠየቁ ይገባል " - ነዋሪዎች
‎"... በየትኛውም መመዘኛ የወጣቶቹ ግድያ ትክክል አይደለም ፤ እውነት ህግ ካለ ርሸና የፈጸሙ አካላት ሊጠየቁ ይገባል " - ነዋሪዎች

ከ13 ቀናት በፊት ‎በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ፦
° ተመስገን ጌታቸው
° ይታገሱ አሰግደው
° ግዛው ግርማዬ የተባሉ ሶስት ወጣቶች በትራንስፖርት እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ከመኪና እንዲወርዱ ተደርገው መገደላቸውን የሚገልፁ መረጃዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ደርሰዋል።

ለ‎ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች ፣ ከስፍራው መረጃ ደረሰን ያሉ እና አካባቢውን የሚያውቁ ታማኝ ምንጮች ሶስቱ ወጣቶች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን #አረጋግጠዋል

‎" በአከባቢው ውጥረት ከነገሰ ውሎ አድሯል " የሚሉት አንድ የአከባቢው ነዋሪ " ላለፉት 6 ዓመታት ገደማ አበሽጌ እና አካባቢው የተረጋጋ ሰላም አልሰፈነበትም " ብለዋል።

" ይህ አካባቢ በኮማንድ ፖስት ስር የሚመራ ፣ ተደጋጋሚ አሰቃቂ ጥቃቶችን የሚያስተናግድ ፤ በአንድ በኩል በታጣቂዎች በሌላ በኩል የታጣቂዎቹን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚወሰድ እርምጃ በመንግስት ፀጥታ ሃይሎች ተፅእኖ የሚደርስበት ፤ ወጣቶች የሚሰደዱበት አከባቢ ሆኗል " ሲሉ አስረድተዋል።

" ሰሞኑን ሶስት ወጣቶች ከመኪና እንዲወርዱ ተደርገው እጃቸው የፊጢኝ ታስሮ በአሰቃቂ ሁኔታ ተረሽነው አስክሬናቸው በትውልድ አካባቢያቸው መገኘቱ እውነት ነው " ብለዋል።

የነዚህ ወጣቶች በፀጥታ ኃይሎች መገደልና ከግድያው በኋላ የሟቾቹ አስከሬን እንዳይነሳ ተብሎ በጅብ እንዲበላ መሆኑ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ፣ ሀዘንና ስጋት መፍጠሩን ተናግረዋል።

" አስክሬናቸው ከሌሊቱ 11 ሰዓት አከባቢ በትውልድ ቀያቸው ተጥሎ ማንም እንዳያነሳና እንዳይቀብራቸው ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በኋላ አስክሬናቸው ለጅብ ተጋልጦ እንዲቆይ ሆኗል። ከሶስቱ የአንዱ ቤተሰቦቹ አንስተው ቀብረዋል " ሲሉ አብራርተዋል።

‎ነዋሪው " ‎'ፋኖ ናቸው' ተብለው ከመኪና እንዲወርዱ ከተደረጉ በኋላ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ነው የሰማነው። ይህ ‎በየትኛውም መመዘኛ ትክክል አይደለም፤ ጥፋትና ወንጀል ፈጽመው ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ ይገባ ነበር። እውነትም ህግ ካለ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን የረሸኑ በህግ ሊጠየቁ ይገባል " ብለዋል።

ሌላው ምንጭ በበኩላቸው፥ " የቱ ቦታ ላይ እርምጃው እንደተፈጸመ በትክክል ባይታወቅም ይህ አሰቃቂ ድርጊት ተፈጽሟል " ሲሉ አረጋግጠዋል።

የተያዙበት ቦታ ከወልቂጤ ወደ ቡታጅራ መንገድ እዣ ወረዳ አገና መሆኑን እንደሰሙ ገልጸዋል።

" እንደ መንገደኛ ሲጓዙ አይደለም የተያዙት " ያለቱ እኚህ አካል " 'ተፈላጊ' ናቸው በሚል የጂፒኤስ ክትትል እየተደረገባቸው ነበር። 'ወንጀል ሰርተው ሲፈለጉ ቆይተው ሊያመልጡ ሲሉ ነው የተያዙት' የሚል ነው ከወረዳው የሰማሁት " ብለዋል።

" ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ለዞን ጸጥታ መዋቅሮች ተነግሮ እነሱም ክትትል እንዲያደርጉ መረጃ ተላልፎ ነበር " ሲሉም አክለዋል።

የተያዙበት ቦታ ላይ ምንም አይነት እርምጃ እንዳልተወሰደባቸው ፤ ከተያዙበት ቦታ በመኪና ይዘዋቸው እንደወጡና እርምጃው ሌላ ቦታ እንደተወሰደ፤ ኋላም አስክሬናቸው በትውልድ መንደራቸው ተጥሎ እንደተገኘ መረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል። አክሬናቸው በተገኘበትና በተያዙበት ቦታ መካከል የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት እንዳለ ጠቁመዋል።

"በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ሁሉን ሰው ያሳዘነና ያስደነገጠ ነው" ብለዋል።

እኚሁ ምንጭ፣ በዞኑ ተደጋጋሚ ችግር ባለባቸው ቦታዎች (አንዱ አበሽጌ) ሰዎች እንደሚገደሉ፣ እንደሚታገቱ፤ ማን ይህንን እንደሚፈጽም በግልጽ እንደማይነገር፤ ነገሮች ተድበስብሰው እንደሚያልፉ ጠቁመዋል።

" አንድ ሰው ወንጀል እንኳን ሰርቶ ቢገኝ በህግ አግባብ ፣ በፍትህ አደባባይ አውሎ ማስጠየቅ እየተቻለ ይህን አይነት እርምጃ መውሰድ ፍጹም ኢሰብዓዊና ተጠያቂነትን ሊያስከትል የሚገባ ነው " ያሉን ሌላኛው ነዋሪ ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን የድርጊቱ ፈጻሚዎች ለህግ ሊቀርቡ ይገባል ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደተረዳው ነዋሪዎች የተጎጂ ቤተሰቦች እየሆነ ያለውን ነገር ወጥተው ለመናገርና መረጃ ለመስጠት ይፈራሉ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፦
° የአበሽጌ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ፣
° የጉራጌ ዞን ሰላምና ፀጥታ ኃላፊ፣
° የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ፣
° የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ስለጉዳዩ ለማነጋገር እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

ፖሊስ አዛዡ እና የአበሽጌ ወረዳ አስተዳዳሪ በተደጋጋሚ የተደወለላቸውን ስልክ አላነሱም።

የጉራጌ ዞን እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ አመራሮች ደግሞ ከተደጋጋሚ ቀጠሮ በኋላ በአካል በመምጣት አልያም " ከኮማንድ ፖስት ውሰዱ " በማለታቸው በዚህ መረጃ ላይ ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።

የክልሉ ምላሽ ?

በትላትናው ዕለት የማዕከላዊ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ለክልሉ ሚዲያዎች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግላጫ ሰጥተው ነበር።

መግለጫው በቀጥታ ከመኪና ላይ ተይዘው ተገድለዋል ስለተባሉት 3 ወጣቶች የሚያብራራው ነገር የለም።

የቢሮው ኃላፊ፣ አጠቃላይ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ እና የመንግስትን አቋም አስረድተዋል።

በመጀመሪያ፥ በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በዋልጋ እና ዳርጌ አካባቢ ነዋሪ ህዝብ ለዘመናት በአብሮነትና አንድነት የኖረ፣ የህብረ ብሔራዊነት እሴት መገለጫ የሆነ ህዝብ መሆኑን አንስተዋል።

" ከዚህ በተቃራኒ ግን ከተለያዩ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር በመቀናጀት ጫካ የገቡ እና እራሳቸውን 'ፋኖ ነን' የሚል ስያሜ የሰጡ ሽፍታዎች በአካባቢው ይገኛሉ " ብለዋል።

" እነዚህ ሽፍታዎች ንብረት ይዘርፋሉ፣ ሰው ይገድላሉ፣ በባህልና በሀይማኖት ፀያፍ የሆኑ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ እንዲሁም የሚያደርሱት ጉዳት ብሔር ተኮር ነው " ሲሉ አብራርተዋል።

ተግባራቸው በሀገሪቱ በሚኖሩ ህዝቦች ላይ አንድነትን የሚፈታተን እና ልዩነትን የሚያጎላ እጅግ አደገኛ ሴራ በመሆኑ፥ መንግስት እስከ ቦታው ድረስ በመሄድ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይቶች ማድረጉን አስታውሰዋል።

በውይይቱም መሰረት፥ አንዳንዶቹ ሽፍታዎች የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ ተጠቅመው የተሃድሶ ስልጠናና ትምህርት ተሰጥቷቸው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ገልጸዋል።

ነገር ግን አንዳንዶቹ አሻፈረኝ በማለታቸው፣ ሳይደክሙ ንጹህ ዜጋን በመግደልና በዝርፊያ መኖርን በመምረጣቸው፣ እንዲሁም በመንግስት ፀጥታ አካላት ላይ ጭምር ጉዳት በማድረሳቸው መንግስት ህገ-መንግስታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከፌዴራል እና ከኦሮሚያ ክልል ጋር በጋራ ህግ የማስከበር ስራዎችን መስራቱን አብራርተዋል።

በዚህም መሰረት፣ " የሰላም አማራጮች አንቀበልም ባሉ እና በታጠቁ ሽፍታዎች ላይ ጥብቅ እርምጃዎች መወሰዱን " ኃላፊው አረጋግጠዋል።

" ይህ ተጨባጭ ሁኔታ እያለ፥ የክልሉን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት የሚሰሩ ኃላፊነት በጎደላቸው ሀሰተኛ ሚዲያዎች የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው " ብለዋል።

" እርምጃው ብሔር ተለይቶ የሚወሰድ ነው ተብሎ የሚወራው አሉባልታ ክልሉን የማይመጥን እና የህዝቦችን የእርስበርስ አንድነት የሚሸረሽር ሆን ተብሎ የተሰራጨ ሀሰተኛ ዜና ነው " ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
ነሐሴ 7 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች