ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#ቤቲንግ

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#ቤቲንግ
#ቤቲንግ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት "በሁሉ ስፖርት" የኦንላይን የስፖርት ውድድር ሎተሪ ሽያጭ (ቤቲንግ) ድርጅት ላይ ተላልፎ የነበረውን የፈቃድ ስረዛ ውሳኔ በሙሉ ድምፅ ሻረው።

• የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ይግባኝ ማቅረቡን ተከትሎ በውሳኔው ላይ ከ 14/11/2018 ዓም ጀምሮ ለ 15 ቀናት የሚቆጠር ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

• "ሁሉ ስፖርት" በከፍተኛ ፍ/ቤት የተፈረደለት ቢሆንም እንኳን የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ ወደ ስራ ሳይገባ የሚቆይ ይሆናል።

(ቲክቫህ ኢትዮጵያ)

የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት የ22 የስፖርት ውድድር ውርርድ ድርጅቶች የስራ ፈቃዳቸው ከህዳር 25 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ የታገደ መሆኑን ለህዝብ ይፋ ባደረገው መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል።

ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግስትን ግብር በመሰወር ወንጀል የተጠረጠሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ፣ በድርጅቶቹ ላይ የተጀመረው የወንጀል ምርመራ እስኪጠናቀቅ በሚል የሥራ ፈቃዳቸው እንደታገደ ይገኛል።

እርምጃው የተወሰደው የተለያዩ የፀጥታ አካላት ባደረጉት የተቀናጀ ክትትልና ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በተገኘ መረጃ መሠረት ነው።

የፈቃድ ስረዛ እርምጃ ከተወሰደባቸው የኦንላይን የስፖርት ውድድር ሎተሪ ሽያጭ (ቤቲንግ) ላይ ከተሰማሩት ተቋማት አንዱ የሆነው በ "ሁሉ ስፖርት" የንግድ ስም የሚንቀሳቀሰው ተቋም " የተወሰነብን ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ መርሆችን የሚጥስ፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ እንዲሁም የአስተዳደር ውሳኔው ከመወሰኑ በፊት የመሰማት መብቴ ተጥሷል " የሚሉ ጭብጦችን በማቅረብ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የፍትሃብሔር ምድብ ችሎት በኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት እንዲሁም በገቢዎች ሚኒስቴር ላይ ክስ በመመስረት ሲከራከር ቆይቷል።

ክርክሩ የተጀመረው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እና የገቢዎች ሚኒስቴር፣ "ሁሉ ስፖርት" (ሁለገብ ኦንላይን ሶሉሽንን ጨምሮ 22 የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች) በከፍተኛ የግብር ስወራ፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር (Money Laundering) እና ተገቢ ያልሆነ የውርርድ አሠራር ውስጥ ተገኝተዋል በሚል የስራ ፈቃዳቸው በቋሚነት እንዲሰረዝ መወሰናቸውን ተከትሎ ነው።

እንደ ተጠሪዎቹ (የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት እና የገቢዎች ሚኒስቴር) ክርክር፣ ድርጅቶቹ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግሥት ግብር እንዲታጣ አድርገዋል።

በተጨማሪም ከተፈቀደው አሠራር ውጭ በበይነ-መረብ (Online) አማካኝነት ሰፊና ሕገ-ወጥ የውርርድ ሥራ ሲያከናውኑ እንደነበርና ይህም በሀገር ደኅንነትና በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ከደኃንነት ተቋማት በደረሰ ጥቆማ ምክንያት የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ መሆኑን በመጥቀስ የፈቃድ ስረዛው ተገቢ እንደሆነ ተከራክረው ነበር።

በሌላ በኩል "ሁሉ ስፖርት" ባቀረበው አቤቱታ፣ የተላለፈበት የፈቃድ ስረዛ ውሳኔ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅን የጣሰ ነው ብሏል።

በተጨማሪም አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ድርጅቱ ጥፋቱ ምን እንደሆነ እንዲያውቅ አልተደረገም፣ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ዕድል አልተሰጠውም እንዲሁም ውሳኔው በበቂ ምክንያትና ማስረጃ ያልተደገፈ ውሳኔ ነው ሲል ተከራክሯል።

ድርጅቱ አክሎም፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ግብር ለመንግሥት ሲከፍል የቆየ እና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ፣ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ በደፈናው "ጥፋተኛ" ተብሎ የንግድ ፈቃዱ መሰረዙ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን የሚጥስ ነው ሲል አቤቱታውን አቅርቧል።

ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ማንኛውንም አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲያስተላልፉ በአዋጅ ቁጥር 1183/2012 የተደነገጉትን መርሆዎች የመከተል ግዴታ አለባቸው ብሏል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ያቀረቡትን "የ100 ቢሊዮን ብር የግብር ስወራ" እና "የህገወጥ ገንዘብ ዝውውር" ክስን በተመለከተ፣ እነዚህ ጉዳዮች በወንጀል ሕግ የሚታዩና በማስረጃ ሊረጋገጡ የሚገባቸው እንጂ፣ በደፈናው ለአስተዳደራዊ ቅጣት (ለፈቃድ ስረዛ) ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም ብሏል።

ተጠሪ መሥሪያ ቤቶች የድርጅቱን ፈቃድ ከመሰረዛቸው በፊት ለድርጅቱ ቅድመ ማስጠንቀቂያ አለመስጠታቸውና ድርጅቱ በጉዳዩ ላይ ያለውን ምላሽ እንዲያቀርብ ዕድል አለመስጠታቸው ጥፋት ነው ብሎታል።

በተጨማሪም ተጠሪዎች(የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት እና ገቢዎች ሚኒስቴር) ከአመልካች (ሁሉ ስፖርት) ፈቃድ የታገደበትና የተሰረዘበትን ምክኒያት አቤቱታ ሲቀርብላቸው ከተጠቀሰው የ100 ቢሊዮን ጉዳት ላይ የአመልካች ምን ያህል ጉዳት አድርሷል የሚለውን በዝርዝር ምላሽ መስጠት ሲገባቸው አለመስጠታቸውን።

ከዛም ባለፈ በአዋጁ መሰረት ቁጥጥር በማድረግ አማራጭ ርምጃዎችም ካሉ እሱን በመከተል ማስተካክል ሲገባ ለቀረበው አቤቱታ ዝምታ መምረጣቸው እንዲሁም ፈቃዱ የተሰረዘበትን አሳማኝ በቂ ማስረጃ በጽ/ቤታቸዉ ጠርተው በማነጋገር፤ በማዳመጥ መልስ መስጠት ሲገባቸው አለመስጠታቸው ተገቢ አይደለም ብሎታል።

ድርጅቱ ፈጸመ የተባለው የወንጀል ድርጊት በሚመለከተው የፍትሕ አካል ተረጋግጦ ሳይቀርብ፣ አስተዳደሩ በራሱ ሥልጣን ፈቃድ መሰረዙ "ከሥልጣን በላይ" የተደረገ ተግባር ነው ተብሏል።

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በድርጅቱ ላይ ያስተላለፈው የንግድ ፈቃድ ስረዛ ውሳኔ እንዲሻር ወስኗል።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው መሥሪያ ቤቶቹ ውሳኔውን ሲያስተላልፉ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግን ያልተከተሉና የተከሳሽን የመሰማት መብት የጣሱ ናቸው በሚል ነው።

የተባለው ድርጊት በተጨባጭ ማድረጉ ሲረጋጠጥ ፈቃድ መሰረዝ ቢችልም በአጠቃላይ በጅምላ ወይም በዘፈቀደ የሁሉንም ስፖርት ውርርድ ላይ የሚሰሩ አመልካችን ጨምሮ ፈቃድ መሰረዝ ፍትሃዊ አይደለም ብሏል።

ተከሳሾች ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ ከፈለጉ ሕግን የተከተለ ሥነ-ሥርዓት እንዲከተሉና የድርጅቱን የመከራከር መብት እንዲያከብሩም ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ አስተላልፏል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ቅሬታ ያለው በመሆኑና ይግባኝ በማለቱ አፈጻጸሙ ከ 14/11/2018 ዓ/ም ጀምሮ ለ 15 ቀናት ለሚቆጠር ጊዜ ታግዶ እንዲቆይ ተወስኗል።

ጉዳዩ በይግባኝ ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት የተመራ በመሆኑ "ሁሉ ስፖርት" በከፍተኛ ፍ/ቤት የተፈረደለት ቢሆንም እንኳን የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ ወደ ስራ ሳይገባ የሚቆይ ይሆናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ከፍርድ ሂደቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶት አገልግሎት የሚሰጥ  ማንኛውም የስፖርት ውርርድ( Sport Betting) ድርጅት የለም በማለት ዜጎች ህገወጥ ውርርድ ከማካሄድ እንዲታቀቡ አሳስቧል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች