ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

ትምህርት ሚኒስቴር ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረጉ የ11 የሥራና ተግባር ትምህርት የሙያ አይነቶችን ዝርዝር አሳውቋል።

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
ትምህርት ሚኒስቴር ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረጉ የ11 የሥራና ተግባር ትምህርት የሙያ አይነቶችን ዝርዝር አሳውቋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረጉ የ11 የሥራና ተግባር ትምህርት የሙያ አይነቶችን ዝርዝር አሳውቋል።

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁለተኛው ዙር ተግባራዊ የሚደረጉ 11 የሥራና ተግባር ትምህርት የሙያ ዓይነቶችን ለመተግበር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት የተመለከተ መመሪያ አስተላልፏል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፓሊሲ ላይ "የሙያና ቴክኖሎጅ ትምህርት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ ከእድሜያቸው ጋር የተመጣጠነ ሆኖ እንዲሰጥ ይደረጋል" በሚል አቅጣጫ መቀመጡን ያመለክታል።

በዚህ መሰረት በየደረጃው የሥራና ተግባር ትምህርት ከሌሎች ትምህርቶች ጋር ተቀናጅቶ እንዲሁም 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ራሱን ችሎ ተማሪዎች በቀጣይ የሚፈልጉትን ሙያ እንዲመርጡ በሚያስችል መልኩ እየተሰጠ ይገኛል ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በ11ኛ እና 12ኛ ክፍል በተለያዩ የሙያ አይነቶች ከቀለም ትምህርታቸው ጎን ለጎን ከ2017 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በ12 የሙያ አይነቶች እየተሰጠ እንደሚገኝም ሰርኩላሩ ያትታል።

ትምህርት ሚኒስቴር ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ደግሞ በሁለተኛው ዙር እንዲተገበሩ ለተለዩት 11 የሙያ አይነቶች ለ11ኛ እና 12ኛ ክፍል መርሐ ትምህርቶች እንዲሁም ለ11ኛ ክፍል የተማሪ ሞጁሎችና የመምህር መምሪያዎች ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።

በመሆኑም እነዚህን ተጨማሪ የሙያ አይነቶች ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በ11ኛ ክፍል ለማስጀመር :-

• የክልሉ/የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ዝርዝር እቅድ በማዘጋጀት እና እቅዱን ለማከናወን በጀት በመያዝ የሙያ አይነቶችን በትምህርት ቤት እና በተማሪዎች ደረጃ በማስመረጥ፣

• የየሙያ አይነቱ መምህራንን በመቅጠር፣

• የመማሪያ ማስተማሪያ ግብዓት በሂደት በማሟላት፣

• መምህራንን እና የትምህርት አመራሮችን በማሰልጠን እና የህዝብ ንቅናቄ ስራዎችን በማከናወን ትምህርቱን ለማስጀመር ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ትምህርት ሚኒስቴር ከ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረጉ የ11 የሙያ አይነቶችን ዝርዝር አሳውቋል።

የሙያ አይነቶቹ ፦
- ብረታ ብረት ሥራ ቴክኖሎጂ፣
- አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ፣
- አልባሳት ቴክኖሎጂ፣
- ህንፃ ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋት፣
- ቧንቧ ስራ፣
- ሶፍትዌር ማበልጸግ፣
- ሰብል አመራረት፣
- ጤና ክብካቤ አገልግሎት፣
- ሆቴል አገልግሎት፣
- ፀጉር ሥራና ውበት አገልግሎት እንዲሁም ምግብ ዝግጅት ናቸው።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች