ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" አባቴን ፖሊስና ሚሊሾች ከቤት መጥተው የወሰዱት ' ለተማሪዎች የተገዛው እህል ተጭኖ መወሰዱን ለምን ለሚዲያ ተናገርክ ? ' ብለው ነው " - የታሳሪ ቤተሰብ

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" አባቴን ፖሊስና ሚሊሾች ከቤት መጥተው የወሰዱት ' ለተማሪዎች የተገዛው እህል ተጭኖ መወሰዱን ለምን ለሚዲያ ተናገርክ ? ' ብለው ነው " - የታሳሪ ቤተሰብ
" አባቴን ፖሊስና ሚሊሾች ከቤት መጥተው የወሰዱት ' ለተማሪዎች የተገዛው እህል ተጭኖ መወሰዱን ለምን ለሚዲያ ተናገርክ ? ' ብለው ነው " - የታሳሪ ቤተሰብ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን ድጉና ፋንጎ ወረዳ፣ አንካ ድጉና ቀበሌ በሚገኘው አንካ ብሳሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም የተዘጋጁ ልዩ ልዩ የምግብ ግብዓቶች ከትምህርት ቤቱ ተጭነው መወሰዳቸውን የአካባቢው ማህበረሰብ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረው ነበር።

አካባቢው በድርቅ መመታቱን ተከተሎ ለተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ከቀረበው ድጋፍ ውስጥ ፦
- ሩዝ፣
- ዘይት፣
- ቦለቄ፣
- ቂንጬ፣
- ስንዴና ጨው ሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ/ም ከሌሊቱ 7:00 ሰዓት ገደማ በሞተር ሳይክሎች ተጭኖ መወሰዱ ይታወቃል።

የድጉና ፋንጎ ወረዳ ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ባዛ በተገኙበት " ለሚዲያ መረጃ ለምን ሰጣችሁ ? በሰዓቱ ለማንም እንዳትናገሩ ብለናችሁስ አልነበረም ወይ ? " በማለት ፦
- የአንካ ድጉና ቀበሌ ሥራ አስኪያጅ አቶ አማኑኤል ኮይሻ
- አቶ ሳሙኤል አልጋ (የቀበሌው ሽማግሌ)፣
- አቶ ሹሚ ኢላሆ እና
- አቶ አሊዬ ቢቢሶ
በዛሬው እለት ከቀኑ 8:00 ሰዓት መታሰራቸውን የቅርብ ቤተሰቦቻቸው እና በሰዓቱ ሲታሰሩ ያዩ የአይን እማኞች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

እማኞቹ እንደሚሉት ከሆነ፣ በቀበሌው ሊቀመንበር አስተባባሪነት ለተማሪዎች የምግባ ፕሮግራም የተገዛው እህል ሲጫን በዕለቱ ያዩትን እና ትክክለኛ መረጃዎችን " ለሚዲያ ሰጥታችኋል " በማለት ከቀበሌው ስራ አስኪያጅ ውጭ ያሉትን በአንካ ድጉና ቀበሌ ፖሊስ ጣቢያ አስረዋቸዋል።

" ቀበሌው ሥራ አስኪያጅ አቶ አማኑኤል ኮይሻን ወደ ወረዳ ከመሸ ወስደዋቸዋል "  ሲሉ አክለዋል።

ቃላቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡ ከአይን እማኝ ምን አሉ ?

" ' እናንተ ናችሁ ለሚዲያ መረጃ የሰጣችሁት፣ ንብረቱ ቢበላ እናንተ ምን አገባችሁ፣ ንብረትነቱ የመንግስት ነው፣ ይህ እህል ከእናንተ ማሳ አልሰጣችሁን፣ ምን ያገባችኋል ? በሰዓቱ አልነገርናችሁም ወይ ከወረዳ መንግስት ጋር ተነጋግረን ነው የምንጭነው ብለን ? እኛ ተናበን ነው የምንሰራው፣ እናንተ ምንም አታመጡም፣ በማያዋጣችሁ ነገር ውስጥ ነው የገባችሁት፣ የእጃችሁን ታገኛላችሁ ' እያሉ አስረው ሲወስዷቸው አይቻለሁ።

' ለሚዲያ ማን መረጃ ስጡ አላችሁ ? ' በማለት ነው ያሰሯቸው። የቀበሌው ስራ አስኪያጅ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አናውቅም። የወረዳው ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ነው በመኪና ይዟቸው የሔደው። ሌሎቹ እዚሁ ቀበሌ ነው የታሰሩት። የቀበሌው ሚኒሾች ግለሰቦቹ በታሰሩበት እየደበደቧቸውና እያስፈራሯቸው ነው " ብለዋል።

ለደህንነቱ ሲባል ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ የታሳሪ ቤተሰብ፥ " አባቴን ፖሊስና ሚሊሾች ከቤት መጥተው የወሰዱት ' ለሚዲያ ለምን ጥቆማ ሰጠህ ? 'ብለው ነው። ለተማሪዎች የተገዛው እህል ተጭኖ መወሰዱን ' ለምን ተናገርክ ? ' " ብለው ነው ያሰሩት " ሲል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንድሰጡን የድጉና ፋንጎ ወረዳ ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ባዛ የጠየቅን ሲሆን ጉዳዩን ከሰሙ በኋላ የስልክ ጥሪያችንን አቋርጠዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች