ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ባሉት 50 ያህል ቀናት ውስጥ ብቻ 15 ሺ እንስሳት በድርቁ ምክንያት ሞተዋል " - የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት (ለቲክቫህ ኢትዮጵያ)

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ባሉት 50 ያህል ቀናት ውስጥ ብቻ 15 ሺ እንስሳት በድርቁ ምክንያት ሞተዋል " - የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት (ለቲክቫህ ኢትዮጵያ)
" ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ባሉት 50 ያህል ቀናት ውስጥ ብቻ 15 ሺ እንስሳት በድርቁ ምክንያት ሞተዋል " - የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት (ለቲክቫህ ኢትዮጵያ)

• በተከሰተው ከባድ የዝናብ እጥረትና ድርቅ ከ95 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል ተብሏል።

በሰሜን ጎንደር ዞን በየዳ ወረዳ ባለፉት ጥቂት አመታት በየተወሰነ ጊዜ ይከሰት የነበረው የዝናብ እጥረት ዘንድሮ በከፋ ሁኔታ ማጋጠሙን ተከትሎ፣ በወረዳው ከሚገኙ 22 ቀበሌዎች መካከል በ18ቱ ላይ ከፍተኛ የድርቅ አደጋ መከሰቱ የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።

የወረዳው የግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ገ/ህይወት በላይነህ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በወረዳው ከሚኖሩ 122 ሺህ ነዋሪዎች መካከል ከ95 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ሃላፊው ገበተለይም በደጋማ አካባቢዎች ቀድሞ መጣል የነበረበት ዝናብ እስከ ሀምሌ 19 ቀን ድረስ በመዘግየቱና አሁንም በተቆራረጠ ሁኔታ በመጣሉ በአካባቢው ግብርና ላይ ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል ብለውናል።

እንደ ጽህፈት ቤቱ መረጃ፣ በወረዳው በዘር ተሸፍኖ ከነበረው 17 ሺ 75 ሄክታር መሬት ውስጥ ከ14 ሺህ 375 ሄክታር በላይ የሚሆነው በድርቁ ምክንያት ተመቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ከ450 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የበቀለው ዘር በመድረቁ ምክንያት ተገልብጦ እንዲታረስ የተገደደ ሲሆን፣ 2 ሺህ 228 ሄክታር የሚሆነው ሰብል ደግሞ ድርቁን ተከትሎ በመጣ የተባይና የበሽታ ወረርሽኝ መውደሙ ታውቋል።

ይህም የአካባቢውን የሰብል ምርት በእጅጉ እንደሚቀንሰውና የቀጣይ ጊዜ የምግብ ዋስትናን አደጋ ላይ እንደሚጥል ገልጸዋል።

የድርቁ አደጋ በሰውና በሰብል ላይ ብቻ ሳይወሰን በእንስሳት ሀብት ላይም ከባድ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ያሉት አቶ ገ/ህይወት ካለፈው ሀምሌ 1/2018 ዓም ጀምሮ ባሉት 50 ያህል ቀናት ውስጥ ብቻ ወደ 15 ሺ በላይ እንስሳት በድርቁ ምክንያት መሞታቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

ይህንን ሁኔታ ተከትሎም፣ እስካሁን ወደ 6 ሺ 550 የሚጠጉ ነዋሪዎች መተዳደሪያ ፍለጋ አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ተለያዩ ቦታዎች መሰደዳቸውንም አክለው ገልጸዋል።

ምንም እንኳን እስካሁን በድርቁ ምክንያት የጠፋ የሰው ህይወት ባይኖርም፣ አሁን ያለው ሰብል በቀጣይ ቀናት በቂ ዝናብ ካላገኘ ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል ተጨባጭ ስጋት አለ ነው ያሉት።

የወረዳው አስተዳደር ችግሩን ለመቋቋም ህዝቡን የማረጋጋትና የእርጥበት ጥበቃ ስራዎችን የመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

"ይሁን እንጂ የችግሩ ስፋት ከወረዳው አቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ፣ የዞንና የክልል ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በአካባቢው ተገኝተው የጉዳቱን መጠን እንዲያጠኑ ተደርጓል" ያሉ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት ለተጎዱ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርጉና ለቀጣዩ አስቸጋሪ ጊዜ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንዲያጠናከሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች