ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

"ከንቲባው በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ነው ያረፈው። ሾፌሩ ግን የመኪና አደጋ በተከሰተበት እለት ወዲያው ነው ሕይወቱ ያለፈው" - አቶ ኃይሉ አዱኛ

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
"ከንቲባው በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ነው ያረፈው። ሾፌሩ ግን የመኪና አደጋ በተከሰተበት እለት ወዲያው ነው ሕይወቱ ያለፈው" - አቶ ኃይሉ አዱኛ
"ከንቲባው በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ነው ያረፈው። ሾፌሩ ግን የመኪና አደጋ በተከሰተበት እለት ወዲያው ነው ሕይወቱ ያለፈው" - አቶ ኃይሉ አዱኛ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን መተሃራ ከተማ፥ የከተማው ከንቲባና አሽከርካሪ ባጋጠማቸው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወታቸው ማለፉን የአካባቢው ነዋሪ እና የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደነገሩንና ከአካባቢው በወጡ መረጃዎች መሰረት፣ የመተሃራ ከተማ ከንቲባ አቶ አዲሱ ዋቆ እና አንድ ሹፌር በደረሰባቸው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ሕይወታቸው አልፏል።

ነዋሪው የሞታቸው ምክንያት ሲያስረዱ፣ "የመኪና አደጋ ነው፤ አረጋግጫለሁ። ከንቲባው አቶ አዲሱ ዋቆ ይባላል፤ በጣም ጥሩ ሰው ነበር። ጳጉሜ 3 ቀን 2018 ዓ/ም ነበር የመኪና አደጋው የደረሰው 'ኢላላ' አካባቢ ከሹፌሩ ጋር እየተጓዙ በነበረበት ወቅት። ሹፌሩ ወዲያውኑ ሞተ፤ ከንቲባው በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ሞተ" ብለዋል።

የአካባቢውን አመራሮች ለጊዜው ማግኘት ባይቻልም፤ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ግን ከንቲባው እና ሹፌሩ በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ማለፉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል።

የመኪና አደጋ የደረሰው ጳጉሜ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ "ከንቲባውና ሾፌሩ ሞቱ በመባሉ ትክክል ነው፤ ከዞኑም አጣርቻለሁ" ብለዋል።

"ከንቲባው በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ነው ያረፈው። እኔም በአካል ሂጄ ጠይቄው ነበር። ኢትዮ ኢስታንቡል ነበር የተኛው። አደጋው ያጋጠማቸው ከመተሃራ ከተማ 5 ኪሎ ሜትር በማይሞላ ቦታ ነው" ሲሉ ነግረውናል።

"ሹፌሩ የመኪና አደጋ በተከሰተበት እለት ወዲያው ነው ሕይወቱ ያለፈው" ያሉት ኃላፊው፣ ከንቲባው ግን ከባድ አደጋ ቢደርስባቸውም በጊዜው ሕይወታቸው ተርፎ እንደነበር ገልጸው፣ አደጋው የደረሰው የነበሩበት መኪና ከቦቴ ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭቶ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ "ከቤተሰብ ጠይቄ እንደተረዳሁት፤ ማን እንደደረበ ባላውቅም አደጋው በመደረብ የመጣ ነው፤ ቦታው ከርቭ ነው። የመደረብ አደጋ ይመስለኛል" ሲሉም ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
መስከረም 13 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች