ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" የዘውዱ ገዳዮች በነጻ መሰናበታቸው 'ዘውዱን ለሁለተኛ ጊዜ እንደመግደል ነው' " - ዘጠኝ ማኅበራት

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" የዘውዱ ገዳዮች በነጻ መሰናበታቸው 'ዘውዱን ለሁለተኛ ጊዜ እንደመግደል ነው' " - ዘጠኝ ማኅበራት
" የዘውዱ ገዳዮች በነጻ መሰናበታቸው 'ዘውዱን ለሁለተኛ ጊዜ እንደመግደል ነው' " - ዘጠኝ ማኅበራት

የ32 ዓመቷ ዘውዱ ሃፍቱን በመግደል የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ያሬድ ገብረስላሴ በላይ እና አንገሶም ሃይለማርያም በነፃ መለቀቃቸውን ተከትሎ 9 የሴቶች መብት እና የፍትሕ ጉዳይ ላይ ሚሰሩ ሲቪል ማኅበራት ተቃውሞ አሰምተዋል።

ዘውዱ ነሐሴ 2015 ዓ/ም በመቐለ ከተማ ከጓደኛዋ ሰምሃል ገብረዝያብሔር ጋር በመንገድ ላይ ሳለች አንድ ተሽከርካሪ አጠገባቸው ይደርሳል። ዘውዱ ተሽከርካሪው ውስጥ ካሉ ሰዎች ጾታዊ ጥቃት ይፈጸምባታል። ይህን ድርጊት ለመቃወም ብትሞክርም ሊለቋት ፈቃደኛ አልሆኑም። በኋላም በያዙት ተሽከርካሪ ገጭተው ገድለዋታል።

በዚህ ጉዳይ ያሬድ ገብረስላሴ በላይ እና አንገሶም ሃይለማርያም ዘውዱ ሃፍቱ ላይ ግድያ ፈጽመዋል በሚል ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የመቐለ ማዕከላዊ ፍ/ቤት የዕድሜ ልክ እስራት ፈርዶባቸው ነበር።

የትግራይ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን በይግባኝ መርምሮ የመጀመሪያውን የጥፋተኝነት ውሳኔ ማጽናቱ ተገልጿል።

የማኅብራቱ የጋራ መግለጫ እንደሚጠቅሰው፣ ያሬድ ገብረስላሴ በላይ ሙሉብርሃን መኮንን ወለገርስ የተባለች ሌላ ወጣት ሴትን በመግደልም ተከሷል ፤ በእሱ ላይ የቀረቡትን ክሶችም ሙሉ በሙሉ አምኖ ተቀብሏል።

አሁን ከዘውዱ ሀፍቱ ግድያ ጋር በተያያዘ  ሁለቱም ፍርደኞች ላይ የተላለፈው የእድሜ ልክ እስራት የጥፋተኝነት ውሳኔ ለመለወጥ የሚያስችል አዲስ ማስረጃ ሳይቀርብ በነፃ መለቀቃቸው ቁጣ ቀስቅሷል።

ማኅበራቱ፣ " የዘውዱ ሃፍቱ ገዳዮች በነፃ መሰናበታቸው እሷን ለሁለተኛ ጊዜ እንደመግደል ነው " ብለዋል።

እንዴት ነጻ ተባሉ ?

ጉዳዩ ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲደርስ፣ ሁለቱ ተከሳሾች ላይ ለመፍረድ ጥቅም ላይ የዋለው ዋናው ኦሪጅናል የስልክ ማስረጃ ከይግባኝ መዝገቡ ውስጥ መጥፋቱ ታወቀ።

ሰበር ሰሚ ችሎቱም በዚህ ምክንያት ጉዳዩን ወደ ቀድሞው ታችኛው ፍርድ ቤት በመመለስ፣ የመጀመሪያው ማስረጃ በትክክል እንዲቀርብና ብቃት ያለው ባለሙያ ማስረጃውን እንዲያብራራ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ሆኖም ይህ ትዕዛዝ ሳይፈጸም 5 ወራት እና ቢያንስ 8 ችሎቶች ማለፋቸውን መግለጫው ያስረዳል።

በዚህ ወቅት የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዙ እንደደረሰው ለፍርድ ቤቱ ቢያሳውቅም ትዕዛዙን ለመፈጸም የሚያስፈልገው ማስረጃ አልቀረበም ተብሏል።

በኋላ በመጀመሪያው ማስረጃ ምትክ የተቃኘ ቅጂ ቀርቦ እንደነበር፤ የዐቃቤ ሕጉም ቢሮ በተመሳሳይ የራሱን ቅጂ እንዳቀረበ ተገልጿል።

የፌዴራል ባለሙያ በመጠቀም ማስረጃውን እንዲያስረዳ በቀረበው ጥያቄ ምትክ በትግራይ ክልል ባለሙያ ተቀይሯል ተብሏል።

ሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. የፖሊስ መኮንን በጽሑፍ ማስረጃው ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል። ከ9 ቀናት በኋላም ፍርድ ቤቱ ይህንን ማብራሪያ በቂ ነው በማለት ሁለቱን ተከሳሾች በነፃ እንዲሰናበቱ ወስኗል።

የትግራይ ፖሊስ እና የአንደኛው ፍርደኛ አባት ላይ የተነሳው ጥያቄ ምንድነው ?

የጋራ መግለጫው የማስረጃው መጥፋትና ለ5 ወራት ሳይቀርብ መቆየት ከትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ጣልቃ ገብነት ጋር በቀጥታ ያያይዛል።

በወቅቱ የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ያገለገሉት ኮሎኔል ገብረስላሴ በላይ (አሁንም የትግራይ ኃይል አመራር ናቸው) የመጀመሪያው ፍርደኛ ያሬድ ገብረስላሴ በላይ አባት መሆናቸውን ማኅበራቱ ጠቅሰዋል።

በግንቦት 2016 ዓ.ም. የፖሊስ መርማሪዎች ፍርድ ቤት " ይፈታ " ያለውን አንድ ተጠርጣሪ ከእስር እንዳይለቀቅ ያቀረቡትን ይግባኝ በተመለከተ፣ ኮሎኔል ገብረስላሴ ይግባኙን እንደጥፋት ለመቁጠር የጉዳዩን ኃላፊ ፖሊስ መኮንን በስልክ " አስፈራርተዋል " የሚል ቅሬታ ቀርቦ ነበር።

የጉዳዩ የሚመለከተው የፖሊስ ክፍልም በወቅቱ በጽሑፍ ቅሬታ ማቅረቡ ተገልጿል።

ይህ ክስተት በዘውዱ ጉዳይ ላይ የሥልጣን ጣልቃ ገብነት ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ ...

ተቋማቱ የዘውዱ ግድያ ብቸኛዋ የዓይን ምስክር ሰምሃል ገብረዝያብሔር ለ8 ወራት ያለ ክስ በእስር መቆየቷን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ግንቦት ወር 2017 ላይ ከደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ የመቐለ ማእከላይ ፍርድ ቤት ጨምሮ በሰባቱ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ዳኞችና ፍርድ ቤቶች ማንኛውም የዳኝነት አገልግሎት ከመስጠት ተቆጥበው/ስራ አቁመውም ነበር።

የጋራ መግለጫውን ያወጡት ዘጠኝ ማኅበራት ምን ጠየቁ ?

- በነጻ እንዲሰናበቱ በተባለው ውሳኔ ላይ በአስቸኳይ ይግባኝ እንዲባል፤

- የመጀመሪያው የስልክ ማስረጃ (ከNISS የመጣው) እና ሰበር ሰሚ ችሎቱ የጠየቀው ብቃት ያለው የፌዴራል ባለሙያ በሙሉ እንዲቀርቡ፤

- ኮሎኔል ገብረስላሴ በጥቅም ግጭት ምክንያት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ እና በተቋማቸው የተፈጸመው የአምስት ወራት መዘግየትና በግንቦት 2016 ዓ/ም የተነሳው የጣልቃ ገብነት ክስ በነፃ አካል እንዲጣራ፤

- በግንቦት 2017 ዓ/ም በፍርድ ቤት ላይ የተፈጠረው መስተጓጎልና በዚያ ምክንያት የተፈጠረው የፍርድ አገልግሎት መቋረጥ በተመለከተ ተጠያቂነት እንዲሰፍን፤

- ሰምሃል ገብረዝያብሔርና ብርቱካን ሃፍቱ፣ እንዲሁም ፍርድ ያስተላለፉ ሁሉም ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎችና መርማሪዎች የጽሑፍ እና ተፈጻሚ የሆነ የጥበቃ ዋስትና እንዲያገኙ፤

- UN Women እና የተመድ የሴቶችና ሴት ልጆች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ልዩ ሪፖርተር ስለዚህ ውሳኔ መቀልበስ ሕዝባዊ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

(መግለጫውን ያወጡ 9 ማኅበራት ዝርዝር ከላይ ተመልከቱ)

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ነሐሴ 8 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች