ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#Egypt

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#Egypt
#Egypt

በግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲ ጥሪ በግብፅ ኒው ኤል-አለሚን ከተማ የግብፅ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጎረቤታች የሆኑት የሱዳን ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ የመሪዎች ስብሰባ ተካሂዶ ነበር።

ስብሰባው ላይ የነበሩት ፦
- የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ
- የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ (በግብፅ አውሮፕላን ተልኮላቸው ወደ ግብፅ የሄዱ)
- የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ
- በሱዳን ከRSF ጋር እየተዋጉ ያሉት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱልፈታህ አልቡርሃን ናቸው።

ግብፅ ከሰበሰበቻቸው በኋላ የጋራ መግለጫ ይፋ ያደረጉ ሲሆን መግለጫው ቀጠናዊ መረጋጋትን የሚሰብክ ቢመስልም፣ በስተጀርባው ግን ቀጠናውን ከኢትዮጵያ ተጽዕኖና ፍላጎት ውጭ ለማድረግ የተሰላ የዲፕሎማሲ ሴራ ነው።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ቀጠናውን በቅርብ የሚከታተሉ የጂኦፖለቲካ ተንታኝ እንደገለጹት፣ ይህ በግብፅ አስተባባሪነት የተደረገው ስብሰባ እና የወጣው መግለጫ ኢትዮጵያን በጂኦፖለቲካዊ አውድ ለመጥለፍ እና የሉዓላዊነትና የልማት እርምጃዎቿን ለማኮላሸት ያለመ ስልታዊ ሸፍጥ ነው።

ተንታኙ ስለ መግለጫው ምን አሉ ?

1. የቀይ ባህር አስተዳደር እና የባህር በር ጥያቄ

መግለጫው " የቀይ ባህር አስተዳደር ጉዳይ የባህር ዳርቻ ሀገራት ብቻ ብቸኛ ኃላፊነት ነው " ይላል ይህ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በንግድም ሆነ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ህጋዊ እና ታሪካዊ ጥረት ለማፈን ያለመ ፖለቲካዊ ሸር ነው።

2. የዓባይ ወንዝ እና የውሃ አጠቃቀም

መሪዎቹ በመግለጫው ዓለም አቀፍ ህጎችን፣ የ"ጉዳት ላለማድረስ" መርህ፣ እንዲሁም "በቅድመ ማሳወቂያ፣ ምክክር እና ስምምነት" የመተባበር ግዴታ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። በተጨማሪም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ነባር የውሃ አጠቃቀም የሚጎዱ ማናቸውም "የአንድ ወገን እርምጃዎችን" እንደሚቃወሙ አሳውቀዋል።

ግብፅ እና ሱዳን "በቅድመ ማሳወቂያ እና ስምምነት" በሚለው ሽፋን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት (በተለይ ኢትዮጵያ) በራሳቸው የተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚወስኑትን ውሳኔዎች የማክሸፍ ወይም የ"ቪቶ" ስልጣን በእጃቸው ለማስገባት ይፈልጋሉ። ይህ ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ የቆየውን ኢ-ፍትሃዊ የውሃ ሞኖፖሊ በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ቋንቋ አስጠብቆ ለመቀጠል የሚደረግ ከንቱ ሙከራ ነው።

መግለጫው የታችኛውን ተፋሰስ አጠቃቀም ብቻ በማጉላት፣ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ከድህነት ለማውጣት እና የኃይል እጥረት ለመቅረፍ የሚያደርጉትን የልማት እንቅስቃሴዎች እንደ "አንድ ወገን እርምጃ" አድርጎ ለማሳየት ይሞክራል። ይህ የኢትዮጵያን ህዝብ የህልውናና ልማት አጀንዳ በአንድ ወገን ጫና ለማቆም የሚደረግ የዘመናት ሴራ ነው።

3. የግብፅ የኢትዮጵያን ጎረቤቶች የመነጠል ሴራ

ግብፅ በተለምዶ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ተጽዕኖ ለማስፋት እና ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ ለመነጠል የምታደርገውን እንቅስቃሴ በዚህ ስብሰባ በድጋሚ አጠናክራ መቅረቧን ይጠቁማሉ።

" የግብፅ አርተፊሻል ጥምረቶች "

ምንምኳ ይህ ውጫዊ ርብርብና ጫና ቢኖርም፣ የኢትዮጵያ አቋም ግን በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመ እንደሆነ ተንታኙ ገልጸዋል።

" ኢትዮጵያ ከማንኛውም ጎረቤት ሀገር ጋር በጋራ ማደግ፣ መከባበር እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንጂ በማንኛውም የውጭ ኃይል ሴራ እና ቅንጅት የምትበገር አይደለችም " ብለዋል።

" ኢትዮጵያ የህዝቧን ጥቅም ለማስጠበቅ የምታደርገው ማንኛውንም ዲፕሎማሲያዊ እና ልማታዊ እንቅስቃሴ በማንም ፈቃድ ላይ የሚመሰረት አይደለም " ያሉት ተንታኙ " የዓባይ ወንዝ ውሃ የሁሉም ተፋሰስ ህዝቦች የጋራ ሃብት እንጂ የአንድ ሀገር ብቻ ሞኖፖሊ ሊሆን አይችልም " ብለዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ከማንም ጋር ለግጭት የሚጋብዝ ሳይሆን፣ ለቀጠናው ሰላም እና ትብብር ቅድሚያ የሚሰጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ቀጠናውን በቅርብ የሚከተሉት እኚህ ባለሙያ፣ " ግብፅ የኢትዮጵያን ጎረቤቶች እየሰበሰበች የምትፈጥራቸው እንደዚህ ዓይነት አርቲፊሻል ጥምረቶች የኢትዮጵያን የድል እና የልማት ጉዞ ፈጽሞ ሊያቆሙት አይችሉም " ሲሉ ገልጸዋል።

" ኢትዮጵያ በታሪኳም ሆነ ዛሬ ላይ በማንኛውም የውጭ ኃይል ግፊት የምትመራ ሳትሆን፣ በራሷ አቅም እና በልጆቿ ጽናት የቆመች ታላቅ ሀገር ናት " ሲሉ ሃሳባቸውን ደምድመዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች