ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#EMA

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#EMA
#EMA

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከ11 መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በሚዲያ ዘርፉ የቁጥጥር፣ የመረጃ ልውውጥና የሕግ ማስፈጸም ሥራዎችን በቅንጅት ለማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ (MoU) ተፈራርሟል።

ስምምነቱ በተቋማቱ መካከል ፈጣንና ዲጂታል የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት በመዘርጋት፣ የቁጥጥርና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በጋራ በመምራት እንዲሁም በሚዲያ ዘርፉ የሕግ ማስፈጸም አቅምን በማጠናከር ሕጋዊነትን፣ የሕዝብ ደህንነትንና ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ዋና ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።

➡️ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት እንዲሁም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት (NISS) ጋር ፦
- ለውጭ ጋዜጠኞች የቪዛ፣ የቅድመ ማጣራት፣ የምዝገባና የፕሬስ ፓስ ሂደቶችን ማሳለጥ፤
- በኤምባሲዎች በኩል ሀገራዊ የሚዲያ ሕጎችንና መመሪያዎችን ማድረስ፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ፤
- በብሔራዊ ደህንነትና ዋና ዋና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ማድረግ፤
- የሚዲያ መሳሪያዎች ደህንነት ማጣራት እና የጋራ ቁጥጥር ስራዎችን ማከናወን በጋራ እንደሚሰሩ በመግባቢያ ሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።

➡️ ከኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ደህንነት አስተዳደር (INSA) እና ከአርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ ኢንስቲትዩት (AI) ጋር፦
- የባለስልጣኑ የኢንፎርሜሽን መረብና ዳታ ቤዝ (data base) ከሳይበር ጥቃት መጠበቅ፤
- የዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራዎችን በማጠናከር ህገ-ወጥ የዲጂታል ይዘቶችን መከታተል፤
- የሚዲያ ሬጉሌሽን (Regulation) አጋዥ የሆኑ የአርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስና IT ሲስተሞችን ማልማትና ማሳለጥ፤ እና የተቋማዊ ኢሜይል ዶመይንና የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ስልጠና መስጠት ነው።

➡️ ከሰነዶች ምዝገባ አገልግሎት፣ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር፦
- የአክሲዮን ዝውውር ሲኖር ቅድሚያ ከባለስልጣኑ የተሰጠ ደብዳቤ መኖሩን ማረጋገጥ፤
- በባለቤትነትና አክሲዮን ዙሪያ ዲጂታል የመረጃ ልውውጥ አሰራር መዘርጋት፤
- የተሰረዙ ወይም የታገዱ ሚዲያዎች ንግድ ፈቃድ ላይ ወዲያውኑ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ፤
- በመገናኛ ብዙኃን ዳታቤዝ እና በንግድ ሲስተም መካከል ትስስር መፍጠር።

➡️ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን (CSO) እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር፦
- የሚዲያ መሳሪያዎች ሲገቡ በባለስልጣኑ መረጋገጣቸውን ማረጋገጥና ኮንትሮባንድን መከላከል፤
- በሲቪል ማህበረሰብ ስም ተመዝግበው ህገ-ወጥ የንግድ ሚዲያ ስራ የሚሰሩትን መቆጣጠር፤
- በህግ ጥሰት አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደባቸው አካላት ላይ የህግ ማስፈጸም ስራ ለመስራት።

➡️ ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጋር ፦

- የሚዲያ የፋይናንስ ጤንነት ማረጋገጥ፤ ሚዲያ በፅንፈኛ ኃይሎች እንዳይጠለፍ ውጤታማ ቁጥጥር ማድረግ፤
- ከብሔራዊ ጥቅም አንጻር ድጋፍና እርዳታዎች በትክክለኛ መንገድ መምጣት እና ጥቅም ላይ መዋልን ለመከታተል እንደሚሰሩ በሰነዱ ተጠቅሷል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ፥ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ በባለድርሻ ተቋማት መካከል ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ማስፈን ከስምምነቱ የሚጠበቁ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ እና የሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ " ፌዴራል ፖሊስ ኔትወርኩን ዘርግቷል፣ ከሀገር ውጭ ሆነው በዲጂታል ሚዲያዎች የሚሰሩትን ሃሰተኛ መረጃ ኔትወርካቸውን እየበጣጠስን ነው " ብለዋል።

አክለው " እነሱ በሚሰጡት አጀንዳ የንጹሃን ህይወት እየጠፋ ነው፣ ይህንን መቆጣጠር ይገባል። ከሰብዓዊነት የበለጠ የለም፣ መዘጋት ያለበት መዘጋት አለበት፣ ይህንን ለማድረግ ዛሬ የተፈራረምነው ሰነድ ከፊርማ ባለፈ ወደ ተግባር አስገብተን ማን ምን እያደረገ መሆኑን መቆጣጠር ይገባል " ሲሉ ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ነሐሴ 7 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች