ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#SocialMedia

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#SocialMedia
#SocialMedia

የኢንስታግራምና ፌስቡክን አሠራር ሊቀይር የሚችል ክስ

ኢንስታግራም እና ፌስቡክን የሚያስተዳድረው ሜታ ታዳጊዎችን ለአደጋ እና ለማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ የሚያጋልጡ አሠራሮችን ተጠቅሟል በሚል ከአሜሪካ 30 ግዛቶች የቀረበበት ክስ በፍርድ ቤት ሊታይ ነው።

ክሱ ከተረጋገጠ በኢንስታግራም እና ፌስቡክ የሚገኙ እንደ 'ላይክ'፣ ኢንፋይናይት ስክሮል፣ አውቶፕሌይ እና ተደጋጋሚ ኖቲፊኬሽን ያሉ ባህሪያት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊደረግ ይችላል።

ክሱ ምን ይላል ?

30ዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች ሜታ ታዳጊዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ ረዥም ሰዓት እንዲቆዩና ደጋግመው ወደ መተግበሪያዎቹ እንዲመለሱ የሚያደርጉ አሠራሮችን በመጠቀም የታዳጊዎችን ደኅንነት አልጠበቀም ሲሉ ይከሳሉ።

በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ አሠራሮች ተጠቃሚዎች አንድ ይዘት ካዩ በኋላ ተመሳሳይ ወይም ሌላ አሳታፊ ይዘት ወዲያውኑ እንዲያዩ በማድረግ ተጠቃሚውን በመተግበሪያው ላይ እንዲቆይ የሚያበረታቱ ናቸው የሚል ክርክር ቀርቧል።

'ላይክ'

ከክሱ ዋና ነጥቦች አንዱ 'ላይክ' ነው። በተለይ ታዳጊዎች የሚያገኙትን የ'ላይክ' ብዛት ከሌሎች ጋር በማወዳደር ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋ ከማኅበራዊ ሚዲያ ምላሽ ጋር እንዲቆራኝ ሊያደርግ ይችላል ተብሏል።

ይህም የብቸኝነት፣ የመገለል ስሜት፣ የሰውነት ገጽታን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት እና ሌሎች አሉታዊ ስሜቶችን ሊያባብስ ይችላል።

'ላይክ' መቁጠር ታዳጊዎችን ወደ ድባቴ እንደሚያስገባ እና ችላ የመባል ስሜት እንደሚፈጥር ጥናቶች ያሳያሉ።

ሜታ ላይ የቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው 'ላይክ' ወደ 'ማኅበራዊ ንጽጽር' የሚያስገባ እና የሰዎችን ዋጋ የሚነሳ ነው።

በክሱ የተጠቀሰች አንዲት ታዳጊ፣ ብዙ የዩቲዩብና ኢንስታግራም አካውንቶችን በመክፈት የምታገኘውን 'ላይክ' በመቁጠር ትጠመድ እንደነበርና ስለራሷ ያላት አመለካከት ከ'ላይክ' ጋር እንደተቆራኘ ተናግራለች። በዚህ ምክንያት ገና በ10 ዓመቷ ወደ ድባቴ ገብታለች።

እንዲቀየሩ የተጠየቁ ባህሪያት

የአሜሪካ ግዛቶቹ ፍርድ ቤቱ ሜታ በታዳጊዎች አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ለውጦችን እንዲያደርግ እንዲያዝ ጠይቀዋል። ከተጠቀሱት ለውጦች መካከል ፦

- ታዳጊዎች የሚጠቀሙበትን አካውንት ቤተሰቦች እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል ሥርዓት ማጠናከር፤

- የማያቋርጥ ኢንፋይናይት ስክሮል አሠራርን መገደብ፤

- አንድን መረጃ አስከትሎ ሌላ ዶፓሚን ሆርሞንን የሚያነቃቃ መረጃ አለመስጠት

- የሰዎችን ገጽታ መለወጥ የሚችለውን ፊልተር ማቆም፤

- የ‘ላይክ’ ቁጥርን እንዳይታይ ማድረግ፤

- ቪድዮዎች በራሳቸው እንዲጫወቱ የሚያደርገውን አውቶፕሌይ ማቆም፤

- ተጠቃሚዎች ብዙ አካውንቶችን እንዳይከፍቱ መገደብ፤

- እንደ ኢንስታግራም 'ስቶሪስ' የሚጠፉ ልጥፎችን ማቆም፤

- ታዳጊዎችን በተደጋጋሚ ኖቲፊኬሽን ወደ መተግበሪያዎቹ እንዲመለሱ የሚያደርጉ አሠራሮችን መቀነስ፤

- ታዳጊዎች የሌሎችን ገጽታ በአርትኦት የሚቀይሩ አንዳንድ ፊልተሮችን እንዳይጠቀሙ መገደብ።

ሜታ ምን አለ ?

ሜታ ክሱን አልተቀበለም። ኩባንያው ታዳጊዎችን ለመደገፍ የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጾ፣ በፍርድ ቤት የቀረቡትን ክሶች በማስረጃ እንደሚቃወም አስታውቋል።

ጉዳዩ ለምን ትልቅ ነው ?

ይህ ክስ ከተለመዱ የገንዘብ ቅጣት ክሶች በላይ ሊሄድ ይችላል። የአሜሪካ ግዛቶቹ ሜታ እስከ 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ቅጣት እንዲጣልበት ጠይቀዋል።

ከዚህ በላይ ግን ዋናው ጉዳይ ሜታ በተጠየቀው መሠረት አሠራሩን እንዲቀይር ከተወሰነ ኢንስታግራምና ፌስቡክ ዛሬ ከምናውቃቸው መተግበሪያዎች በእጅጉ የተለዩ ሊሆኑ መቻሉ ነው።

በተለይም 'ላይክ' የፌስቡክ መሠረታዊ ባህሪ ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል። ይህንንና ኢንፋይናይት ስክሮል፣ አውቶፕሌይ እና ኖቲፊኬሽን ያሉ የተጠቃሚ ተሳትፎን የሚያሳድጉ ባህሪያት በታዳጊዎች ላይ እንዲገደቡ ከተወሰነ፣ ይህ በማኅበራዊ ሚዲያ ንድፍ እና በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ሰፊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

የቀደመ ውሳኔ

ከዚህ ክስ በተለየ ኒው ሜክሲኮ ውስጥ በተካሄደ ሌላ የፍርድ ሂደት ሜታ 942 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተወስኗል።

በዚያ ውሳኔ ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ተጠቃሚዎች ፦
• 'ላይክ' እንዲቆም፣
• ታዳጊዎች እርቃን ምስሎችን እንዳይልኩም ሆነ እንዳይቀበሉ፣
• ከተወሰኑ ሰዓታት ውጭ ኖቲፊኬሽን እንዳይላክ የሚያስገድዱ ለውጦች ተወስነዋል።

ሜታ ግን ይህንን ውሳኔ ተቃውሞ ይግባኝ ጠይቋል። የዚህ ውሳኔ ተፈጻሚነትም በኒው ሜክሲኮ የተገደበ ሲሆን፣ 30ዎቹ ግዛቶች ያቀረቡት አዲስ ክስ ደግሞ ከዚህ የተለየ የሕግ ሂደት ነው።

የሚቀጥለው ምንድን ነው ?

የ30ዎቹ ግዛቶች ክስ የአሜሪካን ሕዝብ ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚወክሉ ግዛቶችን ያካትታል።

በመሆኑም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለሜታ ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊ ሚዲያ ኢንዱስትሪው ሰፊ የሆነ የሕግ አቅጣጫ ሊያስቀምጥ ይችላል።

በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ታዳጊዎችን ከሱስ፣ ከጎጂ ይዘት እና ከሥነ-ልቦናዊ ጫና ለመጠበቅ ምን ያህል ሕጋዊ ኃላፊነት አለባቸው ? የሚለው ጥያቄም የጉዳዩ ዋና ትኩረት  ነው።

መረጃው የቢቢሲ አማርኛ ነው።

ነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች