ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#Oromia

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#Oromia
#Oromia

" መሳሪያ ገዝታችሁ ታጠቁ በሚል በምንም ተዓምር የተሰጠ አቅጣጫ የለም " - ኦሮሚያ ክልል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ

" የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ እና ቄለም ወለጋን ጨምሮ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ዞኖች፣ እድሜያቸውና ጤናቸው የሚፈቅድላቸው አርሶ አደሮች የጦር መሣሪያ ገዝተው እንዲታጠቁና አካባቢያቸውን ተደራጅተው እንዲጠብቁ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል " ሲል ዋዜማ ሬድዮ ዘግቧል።

" የክልሉ መንግሥት የጦር መሳሪያ ገዝተው ለሚታጠቁ አርሶ አደሮች ባስቸኳይ የጦር መሳሪያ ፈቃድ ይሰጣል፤ ጥይትም በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል በማለት የዞኖቹ ባለሥልጣናት ለአርሶ አደሮች እንደነገሯቸው ነዋሪዎች ነግረውናል " ነው ዘገባው የሚለው።

ይህም በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል።

የኦሮሚያ ክልል ስለ ጉዳዩ ምን አለ ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ስለጉዳዩ በኦሮሚያ ክልል በኩል ያለውን ቃል ተቀብሏል።

የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኃይሉ አዱኛ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ " መረጃው የተሳሳተ ነው። የተሳሳተ ብቻም ሳይሆን ኃላፊነት የጎደለው መረጃ ነው እየተሰራጨ ያለው " ሲሉ ተናግረዋል።

" የዜጎችን ሰላምና ደኀንነት የማረጋገጥ ሥራ የመንግስት ነው። የጦር መሳሪያዎችን በብቸኝነት የመታጠቅ ስልጣን ያለው መንግስት ብቻ ነው " ሲሉ አክለው፣ " ስለዚህ እንደዚህ አይነት የተሰጠ አቅጣጫ የለም። ፍጹም ስህተት ነው " ብለዋል።

አቶ ኃይሉ አክለው፣ " ያ ማለት ግን በየአካባቢው ሚሊሻ ይደራጃል፤ በክልሉ ጨፌ የታወጀ ስልጣናን ኃላፊነት አለው። በተመሳሳይ የሚሊሻ ጽሕፈት ቤትም እነዚህን ስራዎች ነው የሚሰሩት " ብለዋል።

እየሰራጨ ያለውን መረጃ በተመለከተ ግን " ለዜጎች የተላለፈ መልዕክት የለም " ሲሉ ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ " እድሜያቸው እና ጤናቸው የሚፈቅድላቸው አርሶ አደሮች የጦር መሳሪያ ገዝተው እንዲታጠቁና አካባቢያቸውን ተደራጅተው እንዲጠብቁ " ባለስልጣናት እንዳዘዙ መረጃ መዘዋወሩን በመጥቅስ፣ ይህን ፈትሻችኋል ? እንደዚህ አይነት ትዕዛዝ ያስተላለፈ አካል ሊኖር የሚችል ከሆነ ማረጋገጫው ምን ሊሆን ይችላል ? እየተሰራጨ ያለው መረጃ ነገ ትክክል ላለመሆኑ ማረጋገጫ አለ ? ሲል ቢሮ ኃላፊውን ጠይቋቸዋል።

አቶ ኃይሉ አዱኛ ምን መለሱ ?

" በግል የታጠቁ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሕገወጡንና ሕጋዊውን የትጥቅ መሳሪያ የያዙትን ለመለየት መንግስት የመመዝገብ ስልጣን አለው። ስለዚህ ባልተመዘገበበት አካባቢ 'ኑ አስመዝግቡ፣ ሕጋዊ አድርጉ' ሊሉ ይችላሉ።

ይሄ ሕጋዊ አሰራር ነው፤ የነበረ ነው፤ ያለ ነው።

ሕገወጡን የትጥቅ የመሳሪያ ወደ ሕጋዊ ማመስመጣት የጦር መሳሪያውን የመቆጣጠር ስልጣንና ኃላፊነት ያለው አካል የሚያደርገው ነው። ያልተመዘገበ የጦር መሳሪያ መኖር የለትም፤ ሕጋዊ የሆነ የጦር መሳሪያ መሆን አለበት።

'ያልተመዘገበ የጦር መሳሪያ ካለ እንድታስመዘግቡ' ብሎ ለማህበረሰቡ የሚያስላልፍ የመንግስት አካል ሊኖር ይችላል። ያን ወደ ሌላ ተርጎሞ የሚወስዱ ካልሆኑ በስተቀር በዚህ ደረጃ ዜጎች ' ታጠቁ ' የሚል መንግስት ያስተላለፈው መልዕክት የለም።

ግን ያልተመዘገበ፣ ፈቃድ የሌለው መሳሪያ ካለ ሕጋዊ እንዲደረግ የማድረግ የመንግስት አካላት አንዱ ተግባር ነው። ለዚህም ወዳልሆነ ተተርጉሞ ሊሆን ይችላል። ያ ደግሞ ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች እንዳይኖሩ ህጋዊ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ኃላፊነት ያለበት አካል ነው የሚያስተላልፈው።

ሕጋዊ ማድረግ የተለመደ ነው፤ አርሶ አደሩ አንዳንድ ቦታ ላይ የሚታጠቅበት ሁኔታ ይኖራል። 'እነጠቃለሁ' ብሎ እንዳይሰጋ ሕጋዊ አድርጎ የራሱን አካባቢ እንዲጠብቅበት የማድረግ ሥራ ይኖራል።

ይሄ ደግሞ አንዱ የሚሊሻም ሥራ ነው። የአካባቢውን ሰላም ይጠብቅበታል፤ ሕጋዊ ያደርገዋል ማለት ነው።

'ሕዝብን ታጠቅ' የሚል መልዕክት ግን አልተላለፈም። ሊተላለፍም አይችልም በዚህ ሁኔታ። የህዝቡን ሰላም የማስጠበቅ ትልቁ ኃላፊነት ያለበት መንግስት ነው። መታጠቅም፣ ኃይልንም በብቸኝነት የመጠቀም መብት ያለው መንግስት ስለሆነ ሕዝብን በጅምላ ታጠቅ የሚባልበት ነገር የለም " ብለዋል።

ሕገወጥ መሳሪያዎችን ሕጋዊ የማድረግ ሥራው አሁን እየተከናወነ ነው ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ የጠየቃቸው አቶ ኃይሉ፣ ይህን ጉዳይ ያነሱት ለምሳሌ እንደዚህ አይነት መልዕክት የሚያስተላልፍ አካል ካለ ምን ማረጋገጫ አለ ? የሚለውን ጥያቄ " አንተ ወደ ሌላ እንዳትወስደው ነው " ብለዋል።

" አሁንም የምደግመው ወደ ሌላ እንዳትወስደው ነው። ለምሳሌ ሕጋዊ ያልሆነ መሳሪያ አርሶ አደሩ ታጥቆ ካለ መልዕክት የሚያስተላልፍ የመንግስት አካል ሊኖር ይችላል። ያ ማለት ግን ታጠቁ ማለት አይደለም። ሕጋዊ እንዲሆን ለማድረግ ነው " ሲሉም ያክላሉ።

እየተሰራጨ ያለው መረጃ ግን "'ገዝታችሁ ታጠቁ' የሚል ነው። ገዝታችሁ ታጠቁ በሚል በምንም ተዓምር የተሰጠ አቅጣጫ የለም። ሊኖር የሚችለው በአካባቢው የታጠቀ አርሶ አደር ካለ ሕጋዊ እንዲያደርግ፣ ሰላሙን በአካባቢው እንዲያስጠብቅ፣ ያ ማለት ከሚሊሻው ጋር ተደራጅቶ የራሱን አካባቢ ደኀንነት ሰላም እንዲያረጋግጥ ማድረግ ነው " ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
መስከረም 6 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች