ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

"አሽከርካሪዎቹ ሕይወታቸው ሳያልፍ በቤተሰቦቻቸው ጥረት በሰላም ተለቀዋል" - ማህበሩ

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
"አሽከርካሪዎቹ ሕይወታቸው ሳያልፍ በቤተሰቦቻቸው ጥረት በሰላም ተለቀዋል" - ማህበሩ
"አሽከርካሪዎቹ ሕይወታቸው ሳያልፍ በቤተሰቦቻቸው ጥረት በሰላም ተለቀዋል" - ማህበሩ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ "ቢላ" በሚባለው አካባቢ ከሳምንት በፊት በርካታ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች በታጣቂዎች ጥቃት ሲቃጠሉ፣ ታግተው ተወስደው የነበሩ አሽከርካሪዎች ከእገታ መለቀቃቸውን የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

የእገታና የቃጠሎ ጥቃቱ የተፈጸመው ጳጉሜ 1/2018 ዓ/ም ሲሆን፣ ጉዳዩን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ማብራሪያ የሰጠን ማህበሩ፣ ሾፌሮቹን "በተኩስ ነው ያስቋሟቸው፤ ተሽከርካሪዎቹ ተቃጥለዋል፤ ታጣቂዎቹ አምልጠዋል" ብሎ፣ ዲያው ስልክ ተደውሎለት ጉዳዩን ለሚመለከተው የመንግስት አካል እንዳሳወቀ ገልጾልን ነበር።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ ከነበሩት አሽከርካሪዎች መካከል የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እንዳሉበት፣ አንዱ ሹፌር በወቅቱ ቢያመልጥም፣ ከስምንት በላይ የሚሆኑት ግን መታገታቸውን አስረድቶ ነበር። የሾፌሮችን ውሎ የሚከታተለው "የሾፌሮች አንደበት" ደግሞ የታጋቾች ቁጥር 14 መሆኑን በወቅቱ ማሳወቁ ይታወሳል።

አሁንስ ምን ተባለ?

የታጋቾቹ ጉዳይ ከምን ደረሰ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር አመራር፣ "ሁሉም ተለቀዋል። ሁሉም በሰላም ወደ ወደቤታቸው ገብተዋል" ብለዋል።

ታግተው የነበሩት በትክክል ቁጥራቸው ስንት ነው? የተለቀቁትስ? በሚል ላቀረብነው ጥያቄ አመራሩ፣ "የኛ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ዘጠኝ ናቸው። ስሌሎቹ አላወኩም። የኮንስትራክሽን መኪናዎችም አብረው ስለነበሩ ምን ያክል እንደታገቱ መረጃው የለንም" ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የታጋቾቹ ብዛት 14 መሆኑ በወቅቱ ሲነገር ነበር፤ "ሁሉም ተለቀዋል" ሲባል፤ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው ሌሎቹም ሾፌሮችም ተለቀዋል? ለሚለው ጥያቄ አመራሩ፣ "በወቅቱ ሪፖርቱ የደረሰን የኛ ሾፌሮች ብቻ ነው እንጅ እኮ የኮንስትራክሽን መኪና እና የሌሎች ሾፌሮችም ይኖራሉ፤ ቁጥሩ እስከ 14 ሊደርስ ይችላል" ብለዋል።

የሌሎች ተሽከርካሪዎች ሾፌሮችም ከእገታ መለቀቃቸውን እንደሰሙ ገልጸው፣ "ሁሉም የተለቀቁት ነው የተባለው፤ የሰማሁት እንደዛ ነው። 'ያልተለቀቀ የለም' ነው ያሉኝ" በማለት ነግረውናል።

አሽከርካሪዎቹ ከእገታ የተለቀቁት ከቀናት በፊት መሆኑን ገልጸዋል። ታጋቾቹ የተለቀቁት ገንዘብ ተከፍሎ ነው ወይስ በምን መልኩ ነው? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ "እሱን አላውቅም። ይህ ለሚዲያ ጥሩፋት መሆን የለበትም" ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የታጋች ቤተሰቦችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባይሳካም እኚሁ የማህበሩ አመራር ግን፣ "ወደ ቤተሰቦቻቸውም እየደወልን እያጣራን ስለነበር ታጋቾቹ ቤታቸው ገብተዋል። ከእገታ የተለቀቁት በምን መልኩ እንደሆነ ግን እኛ መረጃ የለንም" ብለዋል።

ገንዘብ ተከፍሎ ነው የተለቀቁት? የሚለው "ጠቃሚ አይደለም" ያሉት አመራሩ፣ "ዋናው ነገር፥ አሽከርካሪዎቹ ሕይወታቸው ሳያልፍ በቤተሰቦቻቸው ጥረት በሰላም ተለቀዋል" ሲሉም ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች