ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

የአገልጋዮች ቅሬታና የተሰጠ ምላሽ

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
የአገልጋዮች ቅሬታና የተሰጠ ምላሽ
የአገልጋዮች ቅሬታና የተሰጠ ምላሽ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፈረንሳይ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም እና ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን አገልጋዮች " ቅሬታ አለን " ሲሉ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር መጥተዋል።

ቅሬታቸው፣ የደብሩ አስተዳዳሪ እና ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ኃላፊ አዲስ ቤተክርስቲያን ሊሰራበት የተደለደለ ቦታ ያለ ሰበካ ጉባኤውና ማህበረ ካህናቱ እውቅና ጨረታ አውጥተው " ለባለሃብት ለ3 አመት ሽጠዋል " የሚል ነው።

አገልጋዮቹ  " ትልቅ ህንጻ ቤተክርስቲያን ሊሰራ ተደልድሎ የተዘጋጀውን ቦታ፣ ሰበካ ጉባኤና ማህበረ ካህናቱ ሳይወያዩበት ፦
- ለወፍጮ ቤት፣
- ለድርጅት፣
- ለመጋዘንና ለከብት እርባታ በአየር ላይ ጨረታ አውጥተው ሽጠውታል " ብለዋል።

አገልጋዮቹ፣ የቤተክርስቲያኗ ቦታ ምቹ ስላልነበረ አዲስ ህንጻ ለመስራት 500 ሺህ ብር ወጭ ተደርጎ ተጠርጎ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ/ም የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል፤ ዲዛይኑም ተዘጋጅቶ ነበር ብለዋል።

" የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪዎች ግን ' አዲስ ህንጻ ቤተክርስቲያን አያስፈልገም ' በሚል ሸንሽነው ሽጠውታል " ሲሉ ተናግረዋል።

" እኛ ሳናውቅ ሳንወያይበት ጨረታ እንዴት ይወጣል ? የሚል ጥያቄ ስናነሳ 5 ካህናትን ከቤተክርስቲያኗ ታግደዋል፤ 8 አገልጋዮችን ደግሞ አሳስረዋቸዋል። የተቀረነው ደግሞ ከቤተክርስቲያኗ ተባረናል " ሲሉ አክለዋል።

አገልጋዮቹ የልማት ሥራ ተሠርቶ ገቢ እንዲገኝና የደመወዛቸው እንዲሻሻል በተደጋጋሚ ቢጠይቁም " አትናገሩ " የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

" አገልጋይ ሲራብ 'ርቦኛል/ቸግሮኛል' ብሎ መጠየቅ ግዴታው ነው " ያሉት አገልጋዮቹ፣ የኑሮ ችግራቸው እንዲቃለልና ልማት ተሠርቶ ገቢ እንዲገኝ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን አመልክተዋል።

" አልሙልን፤ ካልቻላችሁ ደግሞ ሥልጣናችሁን ለሚመለከተው አካል አስረክቡ በማለት ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ከመስጠት ይልቅ እስር ነው የመጣብን ' ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

" ቤተክርስቲያኗ 2015 ዓ.ም ጥቅምት 27 ከተመሰረተች ጀምሮ ከ1,000 እስከ 1500 ብር እየተከፈለን እያገለገልን ነው። እስካሁን ምንም የደመወዝ እድገት የለም። በዛ ላይ በየትኛውም ደብር በሌለ መልኩ 84 አገልጋይ ተቀጥሯል። ከቤተክርስቲያኗ አቅም በላይ ነው። በኑሮ ውድነት እየተሰቃየን ነው። የሚቀጥሩት በራሳቸው ፍላጎት ነው። ችግር ላይ ነን መፍትሔ ስጡን " ብለዋል።

" ቤተክርስቲያኒቱ ሳትሸጥ፣ ማህበረ ካህናቱም ተፈናቅሎ ከቤተክርስቲያን ርቆ እንዳይሄድ የሚመለከተው አካል ሁሉ ስለ ቤተክርስቲያን፣ ስለ ማህበረ ካህናቱ ስትሉ ድረሱልን " ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

Nb. ቲክቫህ ኢትዮጵያ የቤተክርስቲያኗ ሰበካ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ቦታውን ለሱቅ፣ ለድርጅት እና ለመጋዘን ለ3 አመት ኪራይ ለማጫረት የጨረታ ማስታወቂያ ማውጣቱን ሰነድ ተመልክቷል።

ምን ምላሽ ተሰጠ ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የደብሩን ዋና አስተዳዳሪ መላከ ሰላም ቀሲስ ወልደ ጻድቅ ነጋን በጉዳዩ ላይ አነጋግሯል።

ዋና አስተዳዳሪው በምላሻቸው ቦታው እንዳልተሸጠና የተከናወነው የሱቅ ኪራይ ሂደት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ውሳኔው በግል የተደረገ ሳይሆን በሰበካ ጉባኤ፣ በሀገረ ስብከቱ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ በክፍለ ከተማው እና በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር አካላት እውቅናና ስምምነት የተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም ለሱቅ፣ ለድርጅት እና ለመጋዘን ያወጣችሁትን የጨረታ ማስታወቂያ ተመልክተናል፤ ምንድነው ምላሾት ሲል ጠይቋል።

በምላሻቸው " ጨረታ አልወጣም፣ የተሸጠ ነገር የለም፣ ለሱቅ ብቻ ነው ያወጣነው ማስታወቂያውን " ብለዋል።

አክለው ለድርጅት/ለመጋዘን በሚል የወጣው የመጀመሪያው የጨረታ ማስታወቂያ ጉድለትና ቅሬታ የቀረበበት በመሆኑ እንዲሰረዝ መደረጉን ገልጸዋል።

አሰራሩ ተስተካክሎ ሁለተኛ አዲስ የጨረታ ማስታወቂያ የሚወጣ ይሆናል ብለዋል።

ታሰሩ ስለተባሉት አገልጋዮች ማብራሪያ ሲሰጡ " የታሰሩት በፓትሪያርኩ በክብር የተሾምኩትን እኔን አገልጋዮች ከመንበር ጎትተው አስወጥተው ቢሮ ቆልፈውብኝ ነው። ህጉ በራሱ አሰራር ነው ያሰራቸው " ሲሉ አስረድተዋል።

ስለ አገልጋዮች ደመወዝ በተመለከተ " ረሃቡም፣ ጥሙም አንድ ላይ እኩል ነው፤ እኔም እነሱም ተርበናል። ስለዚህ ይህንን ጥያቄያቸውን በትክክል ተቀብያለሁ፣ እስካሁን ድረስ ደግሞ ቤተክርስቲያኗ ያፈራችውን እየተካፈልን ኖረናል " ሲሉ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ነሐሴ 20 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች