ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" ሁለት ሰላማዊ ወጣቶች ተገድለዋል " - የኮሬ ዞን ነዋሪዎች

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" ሁለት ሰላማዊ ወጣቶች ተገድለዋል " - የኮሬ ዞን ነዋሪዎች
" ሁለት ሰላማዊ ወጣቶች ተገድለዋል " - የኮሬ ዞን ነዋሪዎች

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ጎልቤ ቀበሌ ሁለት ሰላማዊ ወጣቶች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ ከምዕራብ ጉጂ በኩል የመጡ ታጣቂዎች ወደ ኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ጎልቤ ቀበሌ በመግባት፣ በሞተር ሳይክል ወደ ኬሌ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ወጣቶችን ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማ በጥይት ገድለዋል።

ጥቃቱ ቡርጂ ዞንን ከኮሬ ዞን በሚያገናኘው ዋናና ብቸኛ መንገድ፣ በጎልቤ ቀበሌ "ቦኮሶ" በሚባል የዳኖ እና ጎልቤ ቀበሌዎች አዋሳኝ ቦታ መፈጸሙንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የአካባቢው አመራር፣ " መንግስት ባለበት ሀገር በፓርላማ ቢጮህ፣ በየስብሰባው ለዘመናት አልቅሰን ብሶታችንን ብንገልፅ የሚሰማንን አልተገኘም " ብለዋል።

" አሁን ላይ በምዕራብ ጉጂ በኩል የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ሃይል በፈለገው ቦታና ሁኔታ፤ በመርጠውና በፈቀደው ጊዜ ይገድለናል " ሲሉ በምሬት አስረድተዋል።

የኮሬ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምን አሉ ?

የኮሬ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ሲዲሞ ማዳሞ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንዳስረዱት፣ ወጣቶቹ ከጂጆላ አካባቢ በሞተር ሳይክል ወደ ኬሌ ከተማ ሲጓዙ ከምዕራብ ጉጂ በኩል ወደ ኮሬ የገቡ የታጠቁ ኃይሎች "ቦኮሶ" በሚባል አካባቢ ጥቃት ፈጽመው ገድለዋቸዋል።

በአካባቢው ለሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ዘላቂ መፍትሔ ለምን መስጠት አልተቻለም ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላነሳላቸው ጥያቄ ኮማንደር ሲዲሞ ምላሽ እና ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የምዕራብ ጉጂ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ምን አለ ?

የምዕራብ ጉጂ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ዳምባ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንዳሉት፣ አካባቢው "ኦነግ ሸኔ" እንቅስቃሴ የሚያደርግበት በመሆኑ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ይፈጸማሉ። 

ታጣቂው ቡድን አካባቢው ያለውን በረሃ ቤዝ  በማድረግ እና ኮሬንም እንደ ሎጅስቲክስ ምንጭ በማድረግ ጥቃት እንደሚፈጽም ገልጸዋል።

አቶ አየለ በቅርቡ በታጣቂው ቡድን ላይ፣ አመራሮቹን ጨምሮ፣ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

በምዕራብ ጉጂ በቅርቡ በሚሊሻዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሚመለከቱ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎች ሲሰራጩ  እንደነበር፣ ይህ ምን ያህል እውነት እንደሆነ የጠየቅናቸው አቶ አየለ፥ " ጠላት ላይ እርምጃ እየወሰድን ነው፤ እየገደልን ነው፤ ውጊያ ሲካሄድ ከሁሉም ወገን ጉዳት ሊደርስ ይችላል " የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች