ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" በስራችን በርካታ ቤተሰብ አለብን፤ አዳምጡን! " - የታይዋን የገበያ አዳራሽ ነጋዴዎች

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" በስራችን በርካታ ቤተሰብ አለብን፤ አዳምጡን! " - የታይዋን የገበያ አዳራሽ ነጋዴዎች
" በስራችን በርካታ ቤተሰብ አለብን፤ አዳምጡን! " - የታይዋን የገበያ አዳራሽ ነጋዴዎች

👉 " የታሸጉት 30 ሱቆች ናቸው፤ ነጋዴዎቹ የ2018 ዓ.ም ዕዳቸውን ከፍለው ወደ ስራ እንዲመለሱ እንፈልጋለን " - የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን

በድሬዳዋ ከተማ ታሪካዊው 'ታይዋን' የገበያ አዳራሽ በልብስ ችርቻሮ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች፣ የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ "በጅምላ ቫት (VAT) ካልገባችሁ" በማለት ሱቆቻቸውን ከሰኔ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ አሽጎባቸው ከስራ ውጪ መሆናቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ።

" 120 ይሆናል የታሸጉት ሱቆች " ያሉት ነጋዴዎቹ ቅሬታቸውን ይዘው የሄዱባቸው የተለያዩ የመንግስት ቢሮዎች ምላሽ እንደነፈጓቸው ጠቅሰዋል።

የፌደራል እና የከተማው አስተዳደር ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ የታሸጉ ሱቆቻቸው እንዲከፈቱ፣ ገቢያቸውን ያገናዘበ ህጋዊ ግብር እየከፈሉ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ጠይቀዋል።

ነጋዴዎቹ በዝርዝር ምን አሉ ?

" የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ ያሸገብን ' ሁላችሁም ቫት መግባት አለባችሁ ' ብሎ ነው።

ቫት ለመግባት አዋጁ አንድ ነጋዴ ቢያንስ አመታዊ ገቢው ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል። ቢሮው አጠናሁት ባለው መሰረት ገቢያችን ከ1.5 ሚሊዮን በታች ነው።

ለምን ሱቃችን ይታሸጋል ስንል ' ገቢያችሁ ከሁለት ሚሊዮን አልፏል፣ ስለዚህ ሁላችሁም በጅምላ ቫት መግባት አለባችሁ ' ነው የሚሉን።

እኛ ደግሞ በሰራነው መጠን ግብር እየከፈልን ነው፣ ያለአግባብ እኛን የሚያከስር እና ከስራ ውጭ የሚያደርገንን ግብር እንድንከፍል ልንጠየቅ አይገባም። ከህግ ውጭ 'በግዳጅ ቫት ካልገባችሁ' ተብሎ ሱቆቻችንን ማሸግ ይቁምልን ብንልም፣ ከወራት በላይ በየቢሮው ብንመላለስም መፍትሄ ሊሰጠን የሚችል አንድም አካል ልናገኝ አልቻልንም።

በአዲሱ የግብር አከፋፈል አዋጅ ቁጥር 1395/2017 መሠረት እስከ 2 ሚሊዮን ብር ድረስ የንግድ እንቅስቃሴ ያላቸው 9% ይክፈሉ ቢልም፣ የኛ መረጃ በእጃቸው እያለ 'ሁላችሁም በጅምላ ቫት ካልገባችሁ በስተቀር አንሰማችሁም' በማለት ከስራችን በማፈናቀል ሱቆቻችንን አሽገውብን ይገኛሉ።

ቫት መግባት የእኛ አቅማችን አይችልም፣ ችርቻሮ ነው የምንሰራው፤ በዛ ላይ ማወራረጃ ሪሲት አናገኝም፣ ስለዚህ በምን እናወራርዳለን ? ሁለተኛ ነገር ደግሞ በጅምላ እንዴት ይገባል ? የአንዱ ቤት ካፒታል ትንሽ ነው፣ የአንዱ ቤት ደግሞ ትልቅ ነው፤ እንዴት በጅምላ ይሆናል? እዩልን ስንል እናንተ ራሳችሁ ይቻላል የምትሉትን ነጋዴ ለይታችሁ ስጡን አሉ።

እናንተ እጃችሁ ላይ ዶክመንት አለ፣ በዛ መሰረት ቫት ይቻላል የምትሉትን ነጋዴ አስገቡ እንጂ እኛ መርጠን አንሰጥም። ምክንያቱም በምንም ማወቅ አንችልም አልን። ' ትገባላችሁ ትገባላችሁ ' ነው መልሳቸው።

የሚመለከተው የከተማውም ሆነ የፌደራል ተቋም ይህን አሳሳቢ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ፍትሃዊ ምላሽ እንዲሰጠን፣ የታሸጉ ሱቆቻችን እንዲከፈቱልን እና ወደ ስራችን እንድንመለስ ይደረግልን።

ስራችንን እንስራ፤ ተገቢና ገቢያችንን ያማከለ ህጋዊ ግብር እንክፈል። አዳምጡን፣ በስራችን በርካታ ቤተሰብ አለብን " ብለዋል።

አንድ ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች ነጋዴ " እኔ በበኩሌ ቫት ለመግባት አቅሙ የለኝም፣ ዕቃዬም ቢታይ አይሆንም። 7 ቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ፣ ከወር በላይ ስራ ማቆም ማለት ከባድ ነው። ስራ ቦታም መኖሪያዬም ተከራይቼ ነው። ያሉሁበት ሁኔታ በጣም ከባድ ነው። ለልጆቼ ዳቦ መግዣ እስከማጣት ደርሻለሁ። መድኃኒት ሊቋረጥባቸው የማይገቡ ቤተሰቦች አሉን፣ ስለዚህ መንግስት እኛ ነጋዴዎች እየራበን እና ኑሮ እንደከበደን አውቆ መፍትሔ ይስጠን " ስትል ትጠይቃለች።

የከተማው ገቢዎች ባለስልጣን ምን መለሰ ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ስለ ጉዳዩ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር ዶ/ር አብዱሰላም መሀመድን አነጋግሯል።

" ' 120 ሱቆች ታሽገዋል ' የተባለው ውሸት ነው 30 አካባቢ የሚሆኑት ናቸው የታሸጉት፣ የታሸጉትም ለአቅመ ቫት የደረሱ ስለሆነ ወደ ቫት መግባት ስላለባቸው ነው " ሲሉ ከነጋዴዎች ለተነሱት ቅሬታዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

አክለውም " የአንድ ነጋዴ የቀን ሽያጩ ከ3000 በላይ ከሆነ ቫት መመዝገብ እንዳለበት ህጉ ያዛል። አንዳንዶቹ የታሸገባቸው ነጋዴዎች በቫት ብቻ ሳይሆን የ2018 ዓ.ም የገቢ ግብር ያልከፈሉ ናቸው። ያ ማለት ዕዳ አለባቸው " ብለዋል።

" መጀመሪያ አካባቢ ከ100 በላይ ሱቆች ታሽገው ነበር። ወዲያውኑ ተነጋግረን ቫት ለመመዝገብ ፍቃደኛ የሆኑት ከ15 ቀን በፊት ተከፍቶላቸው እየሰሩ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

" እንደቢሮ ጥናት አጥንተን ነው እየሰራን ያለነው። ሱቆች እንዲታሸጉ አንፈልግም። ነጋዴዎቹ እየመሰላቸው ያለው ሁለት ሚሊዮን ሲባል ተቀማጭ ገንዘብ ነው። እውነታው ግን አመታዊ ትራንዛክሽን ነው። በነጋዴዎች ላይ የግንዛቤ እጥረት ስለተፈጠረ ነው እዚህ የደረስነው " ሲሉ አስረድተዋል።

" ከነጋዴዎች ጋር አሁን መግባባት ላይ እየተደረሰ ነው " የሚሉት ዶ/ር አብዱሰላም መሀመድ " ሃሳባችን ህጋዊ ግብይት እንዲኖር ነው፣ በታይዋን ገበያ አዳራሽ አካባቢ ኮንትሮባንድ ንግዶች ተንሰራፍተዋል፣ ስለዚህ ለሚሸጡት እቃ ደረሰኝ መስጠት አለባቸው ነው " ያሉት።

" አሁን ላይ ሱቃቸው የታሸገባቸው ነጋዴዎችንም አወያይተናል። ቅሬታ ካላቸው ቅሬታ ሰሚ አለ፣ ቅሬታቸውን ማቅረብ ይችላሉ፣ ሱቆች ሲዘጉ ነጋዴዎች ብቻም ሳይሆኑ መንግስትም ተጎጅ ነው። እኛ የምንፈልገው ነጋዴዎቹ ወደስራ እንድመለሱ ነው " ብለዋል።

" እንዳይሰሩ ማድረግ የገቢ ግብር አዋጁ መርህ አይደለም። አዋጁን ተገንዝበው ያለባቸውን ዕዳ ከፍለው ወደ ስራ መግባት አለባቸው " ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች