ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

ኢትዮ ቴሌኮም በ2019 በጀት ዓመት 295 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ገለጸ።

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
ኢትዮ ቴሌኮም በ2019 በጀት ዓመት 295 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ገለጸ።
ኢትዮ ቴሌኮም በ2019 በጀት ዓመት 295 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ገለጸ።

ኩባንያው በበጀት ዓመቱ 43.1 ቢሊዮን ብር የትርፍ ክፍፍል ለማበርከት ማቀዱንም ይፋ ተደርጓል

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር 2028” (Lead the Future: Digital and Beyond 2028) የተሰኘውን የሶስት ዓመታት ስትራቴጂ ሁለተኛ ዓመት (የ2019 በጀት ዓመት) ዓመታዊ የቢዝነስ እቅድ በዛሬው እለት በዝርዝር አቅርበዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚዋ እንደገለጹት "የስትራቴጂያችን ዋነኛ ግብ ኩባንያችንን ከመደበኛ የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ወደ ሁለንተናዊ የቴክኖሎጂ ኩባንያ (Telco-to-TechCo) ማሸጋገር ነው" ብለዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገለጻ ኩባንያው በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ አመታዊ ገቢው 295 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅዷል ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ36.7 በመቶ ወይም የ79.2 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ተብሏል።

ከዚህ ገቢ ውስጥ 26.3 በመቶው (77.45 ቢሊዮን ብር) ከዲጂታል እና ተያያዥ የቢዝነስ ዘርፎች የሚገኝ ነው።

በተጨማሪም 253.7 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማመንጨት መታቀዱንም ተገልጿል።

የኩባንያው አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር በ6.7 በመቶ እድገት አሳይቶ 96.2 ሚሊዮን እንዲደርስ ግብ ማስቀመጡን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ይፋ አድርገዋል።

በተጨማሪም :-

- የሞባይል ድምፅ ተጠቃሚዎች 92.3 ሚሊዮን፣

- የሞባይል ዳታ እና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 60.01 ሚሊዮን፣

- የፊክስድ ብሮድባንድ ደንበኞች ደግሞ 1.26 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል።

- የ4ጂ (LTE) ጣቢያዎችን ቁጥር ከ6,924 ወደ 11,014 በማሳደግ የሕዝብ ስብጥር ሽፋኑን 95 በመቶ ለማድረስ

- የ5ጂ አገልግሎትን በ73 ከተሞች በማስፋፋት የጣቢያዎቹን ቁጥር 648 ለማድረስ፤

- የገጠር ተደራሽነትን ለማስፋት 1,685 አዳዲስ ሳይቶችን በመገንባት 4.5 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል።

- በበጀት አመቱ የዓለም አቀፍ የመረጃ መተላለፊያ (International Gateway) አቅምም ወደ 5.2 Tbps ከፍ ይላል ተብሏል።

- የቴሌብር ደንበኞችን ቁጥር 67.69 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፣ በዓመቱ ውስጥ 7.4 ትሪሊዮን ብር ዝውውር (Transaction volume) ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

- ዲጂታል ፋይናንስን በተመለከተ 33.08 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እና 26.42 ቢሊዮን ብር የቁጠባ መጠን ለማድረስ ግብ ተቀምጧል።

- የ"ዘመን ገበያ" የኢ-ኮመርስ ፕላትፎርም 1.4 ቢሊዮን ብር የግብይት ዋጋ (GMV) እንዲያስመዘግብ ታቅዷል።

- ኩባንያው በተጨማሪም 2.6 ሚሊዮን የኮኔክቲቪቲ ዲቫይሶችን ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 1 ሚሊዮን የሚሆኑት ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ክላውድ ቤዝድ "ዘኔክሰስ" (Nexus) ስማርት ስልኮች ናቸው ተብሏል።

በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ 43.1 ቢሊዮን ብር የትርፍ ክፍፍል (Dividend) እና 83.8 ቢሊዮን ብር ግብር ለሀገር ገቢ ለማድረግ ማቀዱን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አሳውቀዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች