ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

የስፖርት ውርርድ በአዲስ የቁጥጥር ሥርዓት ዳግም ሊጀመር ነው።

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
የስፖርት ውርርድ በአዲስ የቁጥጥር ሥርዓት ዳግም ሊጀመር ነው።
የስፖርት ውርርድ በአዲስ የቁጥጥር ሥርዓት ዳግም ሊጀመር ነው።

የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት፣ የስፖርት ውርርድ እንቅስቃሴ በአዲስ የቴክኖሎጂና የቁጥጥር ሥርዓት ከተዋቀረ በኋላ ዳግም እንደሚጀመር አስታውቋል።

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቤዛ ግርማ ለኢቢሲ እንደገለጹት፣ የስፖርት ውርርድ መቆሙ ዘርፉን ወደ ጠንካራ የሕግና የቁጥጥር ሥርዓት ለማስገባት ከተወሰደው የሪፎርም እርምጃ ጋር የተያያዘ ነው።

አዲሱ አሠራር ከ " ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 " ስትራቴጂ ጋር በተጣጣመ መልኩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የቁጥጥር ሥርዓት ይኖረዋል ብለዋል።

በዚህም መንግሥት የኦፕሬተሮችን የፋይናንስና አጠቃላይ እንቅስቃሴ በቀጥታ መከታተል የሚያስችለው ሥርዓት እንደሚዘረጋ ገልጸዋል።

የዳግም ማስጀመሩ ዝግጅት የተነሳው በቀድሞው አሠራር የታዩ የፋይናንስና የቁጥጥር ችግሮችን በመመርመር መሆኑ ታውቋል።

አገልግሎቱ ባካሄደው ምርመራ፣ ፈቃድ ያላቸው የስፖርት ውርርድ ኦፕሬተሮች የፋይናንስ ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው መንግሥት ማግኘት የነበረበት 27.5 ቢሊዮን ብር ገቢ እስካሁን እንዳልተሰበሰበ አስታውቋል።

ወ/ሮ ቤዛ እንደገለጹት፣ ኦፕሬተሮቹ ባንቀሳቀሱት 199 ቢሊዮን ብር ላይ 30 ቢሊዮን ብር የኮሚሽን ክፍያ ይጠበቅባቸው ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን የተከፈለው 3.6 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው።

ከዚህ ያልተሰበሰበ ገቢ ውስጥ 8.64 ቢሊዮን ብር በ "ዳሽ ቤት" የስፖርት ውርርድ ድርጅት ላይ የተከማቸ ዕዳ መሆኑን ረቂቅ የኦዲት ሪፖርት እንደሚያመለክት ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ይህ ረቂቅ የኦዲት ሪፖርት መሆኑን ገልጾ፣ የመጨረሻ የኦዲት ውጤቱ ከተረጋገጠ በኋላ ያልተከፈለውን ገቢ ለማስመለስ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።

በተጨማሪም፣ የዲጂታል ሎተሪ አገልግሎትን በሚመለከት ከግል አጋር ጋር የነበረው ስምምነት፣ በውሉ የተቀመጡ የቴክኖሎጂና ሌሎች ግዴታዎች ባለመሟላታቸው መቋረጡን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

አዲሱን የቁጥጥር ሥርዓት ለማጠናከርም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሥራ ልምድ ያላቸው አዲስ የፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ መመደባቸው አመልክተዋል።

በአሁን ወቅት የኦፕሬተሮች ፈቃድ ከተሰረዘ በኋላ የቀጠሉ ሕገ-ወጥ የውርርድ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም አገልግሎቱ ከፀጥታ፣ ከፋይናንስና ከቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

አገልግሎቱ ሕጋዊ ፈቃድ በሌላቸው የስፖርት ውርርድ መድረኮች ላይ ህብረተሰቡ እንዳይሳተፍና ምንም ዓይነት የገንዘብ ግብይት እንዳይፈጽም ለኢቢሲ በሰጠው ቃል አሳስቧል።

መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች