ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን የደረጃ እድገት አፈጻጸም መመሪያን ይፋ አደረገ።

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን የደረጃ እድገት አፈጻጸም መመሪያን ይፋ አደረገ።

የትምህርት ሚኒስቴር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ በሚያስተምሩ መምህራን ላይ ተፈጻሚ የሚሆን "የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን የደረጃ እድገት አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1148/2018" አውጥቷል።

ሚኒስቴሩ በአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1368/2017 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ያዘጋጀው ይህ መመሪያ፣ በማስተማር ሥራቸው የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ መምህራንን ለማበረታታት፣ የሥራ ተነሳሽነታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም አጠቃላይ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በመመሪያው ድንጋጌ መሠረት የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን የእድገት መሰላል በሰባት ደረጃዎች የተከፋፈለ ሲሆን፤ እነሱም ፦
- ጀማሪ መምህር፣
- መለስተኛ መምህር፣
- መምህር፣
- ከፍተኛ መምህር፣
- ተባባሪ መሪ መምህር፣
- መሪ መምህር እና ከፍተኛ መሪ መምህር ናቸው።

በመመሪያው የተቀመጠው የቆይታ ጊዜም ከጀማሪ ወደ መለስተኛ መምህርነት ለመሸጋገር 2 ዓመት፣ በቀጣዮቹ ደረጃዎች ደግሞ በእያንዳንዱ እርከን የ3 ዓመታት ቆይታ የሚጠይቅ ነው።

ይሁን እንጂ አንድ መምህር በተከታታይ ወይም በተለያየ ጊዜ በውድድር ሁለት ጊዜ እድገት ማግኘት ካልቻለ ለሦስተኛ ጊዜ የመወዳደር ዕድል እንደማይኖረው በመመሪያው ተደንግጓል።

መምህራን ለደረጃ እድገት ውድድር ብቁ ለመሆን ማሟላት ከሚገባቸው የጋራ መስፈርቶች መካከል በመምህርነት ሙያ ዕውቅና ካለው ተቋም የተመረቁ መሆን፣ የሙያ ፈቃድ ምስክር ወረቀት መያዝ፣ እንዲሁም ለጀማሪ መምህራን የመውጫ ምዘና ማለፍ በዋናነት ተቀምጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አንድ መምህር ለደረጃ እድገት ለመብቃት ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች ውስጥ ቢያንስ 75 በመቶ የሚሆኑት 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸው በገለልተኛ አካል መረጋገጥ እንዳለበት ሰነዱ ያትታል።

በተጨማሪም ጀማሪ መምህራን ቢያንስ የ40 ሰዓታት፣ ከመለስተኛ መምህር ጀምሮ ያሉት ደግሞ የ60 ሰዓታት ሙያ ተኮር አጫጭር ሥልጠናዎችን መከታተልና የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ (CPD) ዕቅዳቸውን በአግባቡ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል።

ወደ ከፍተኛ የእድገት እርከኖች ለመሸጋገር የተቀመጡት መመዘኛዎች የማስተማር ብቃትን ብቻ ሳይሆን የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎንም ያካተቱ ናቸው።

በዚህም መሠረት መምህራን ከደረጃ ወደ ደረጃ ሲሸጋገሩ ከ70 እስከ 90 በመቶ የሚደርስ የሥራ አፈጻጸም ውጤት ማስመዝገብ፣ የተደራጀ ማኅደረ-ተግባር (Portfolio) መያዝ፣ ጀማሪ መምህራንን በአማካሪነት መደገፍ እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያላቸውንና ተጋላጭ ተማሪዎችን መርዳት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

በተለይም ከመካከለኛ ደረጃ ጀምሮ ባሉት ከፍተኛ እርከኖች ለመወዳደር የመማሪያና የመምሪያ መጻሕፍትን መገምገም፣ አጋዥ የትምህርት ጽሑፎችን ማዘጋጀት እና በመማር ማስተማር ችግሮች ዙሪያ ተግባራዊ ጥናትና ምርምሮችን (Action Research) ማካሄድ የግድ እንደሚል ሰነዱ በዝርዝር አስቀምጧል።

አዲሱ መመሪያ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መምህራን የተፋጠነ የደረጃ እድገት የሚሰጥበትን አሠራርም አስተዋውቋል።

በዚህም መሠረት ከመምህርነት እስከ መሪ መምህርነት ባለው እርከን የሚገኝ ማንኛውም መምህር የሚያስተምራቸው ተማሪዎች በሙሉ 85 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት በተከታታይ ሁለት ዓመታት እንዲያስመዘግቡ ካደረገ እና ይህም በገለልተኛ አካል ሲረጋገጥ፣ የሦስት ዓመት የቆይታ ጊዜውን ሳይጠብቅ በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲያድግ ይደረጋል።

በተመሳሳይም የተማሪዎቹን ውጤት 90 በመቶ እና ከዚያ በላይ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ያደረሰ መምህር አንድ የደረጃ መሰላል ዘሎ እንዲያድግ የሚፈቀድ ሲሆን፤ በከፍተኛ መሪ መምህርነት ደረጃ ላሉት ደግሞ የሁለት እርከን ደመወዝ ጭማሪ እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል መመሪያው የወሊድ ፈቃድ ላይ ያሉ መምህራንን፣ በጤና እክል ምክንያት በቦርድ ውሳኔ ከክፍል የተገለሉ ባለሙያዎችን እና በመምህራን ማኅበራት በአመራርነት የሚያገለግሉ አባላትን የደረጃ እድገት አፈጻጸም በልዩ ሁኔታ አካቷል።

የደረጃ እድገቱ በየዓመቱ በሁለት ዙር ማለትም በጥር አንድ እና በሐምሌ አንድ ቀን ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ ሂደቱም በትምህርት ቤት ቴክኒክ ኮሚቴና በደረጃ እድገት ኮሚቴ ተጣርቶ በወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት አማካይነት ይጸድቃል።

አሠራሩ ፍትሐዊና ገለልተኛ እንዲሆን የጥቅም ግጭትን የሚከላከሉ ድንጋጌዎች የተካተቱበት ሲሆን፣ በውሳኔው ላይ ቅሬታ ያላቸው መምህራንም ደብዳቤው በደረሳቸው በ10 የሥራ ቀናት ውስጥ አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችሉ ተደንግጓል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
መስከረም 17 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች