ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#BenishangulGumuz

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#BenishangulGumuz
#BenishangulGumuz

በታጣቂዎች የተደጋገመ ጥቃት እያስተናገደ በቀጠለው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን የታጠቁ ኃይሎች ባደረሱት አዲስ ጥቃት ተሳፋሪዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተሰምቷል።

አንድ የማንድራ ወረዳ ሠራተኛ፣ ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ እየተጓዘ የነበረ ህዝብ ያሳፈረ አባዱላ ተሽከርካሪ ላይ ታጣቂዎች ከትናንት በስቲያ ጥቃት ማድረሳቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

" የችግሩ ፈጣሪዎች ማን እንደሆኑ አናውቅም " ብለዋል። " በጥቃቱ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል። አራት ቆስለዋል " ሲሉ ገልጸዋል።

በወቅቱ የሚያውቋቸው የፖሊስ አባል በቦታው ተገኝተው እንደነበር ገልጸው፣ ጥቃት ስላደረሱት አካላት ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ፤ ቦታው ከዚህ በፊትም ሁለት ጊዜ ጥቃት እንዳጋጠመ አመልክተዋል።

መስከረም 14/2019 ዓ/ም ማንዱራ ሳይደርስ ግልገልበለስ ወረዳን አለፍ ብሎ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ደርሶ አንድ ሰው ሲገደል፣ ስድስት መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ነዋሪዎችና ከቦታው የወጡ መረጃዎችም ከሟቾች ባሻገር ታግተው የተወሰዱ እንዳሉ ጠቁመዋል።

የክልሉ ም/ቤት አባል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አሉ ?

ሰሞንኛውን አዲስ ጥቃት በተመለከተ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የክልሉ ም/ቤት የፍትህ፣ የሰላም እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ አቶ ግራኝ ጉዴታ አናግሯል።

ማንዱራ ወረዳ ጥቃት ስለመፈጸሙ ከስፍራው ተደውሎ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

" መንግስት የነገሩን መነሻ ፈልጎ መፍትሄ መስጠት፣ ህዝቡን ማረጋጋት ሲገባው ለምን ዝምታ መረጠ ? እናንተስ ለምን ዝም አላችሁ? " የሚል ጥያቄ ከነዋሪዎች እንደቀረበላቸው ገልጸዋል።

" መንግስት የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ፤ ለሚከሰተው ችግር ቶሎ መፍትሄ መፈለግ፤ ወንጀለኞችን ፈልጎ ለሕግ የማቅረብ ኃላፊነት አለበት። ዝምታ ተገቢ አይደለም " ሲሉ አሳስበዋል።

በጥቃቱ ንጹሐን ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

📞 የማንድራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቤዋ ቡልት ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፣ ጉዳዩን ከሰሙ በኋላ ማብራሪያ በመስጠት ፈንታ ስልክ ዘግተዋል፤ ድጋሚ ሲደወል አያነሱም።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን መለሰ ?

የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ ምን ምላሽ እንዳላቸው፣ መሰል ጥቃቶች ለማስቆም ምን እየተሰራ እንደሆነ የጠየቅናቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ፣ " ጉዳዮቹን እያጣራን ነው " ብለዋል።

" አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ስላለ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃቶች ለማድረስ ጥረት የሚያደርጉበት ሁኔታዎች አሉ " ብለዋል።

" ይህን ለማስተካከል የክልሉ መንግስት ከውይይት ጎን ለጎን በየአካባቢው በቂ ኃይል እንዲመደብ መስራት ያለብን ሥራ እየተሰራ ስለሆነ በአጭር ጊዜ መስመር ይይዛል " ነው ያሉት።

ታግተው የተወሰዱትን ለማስለቀቅ ምን ጥረት ተደረገ ? የሟቾች ቁጥር ስንት ነው? ስንል ላቀረብነው ጥያቄ፣ " ሥራ እየተሰራ ነው የሟቾች ቁጥር ገና አልተረጋገጠም። በአጠቃላይ ቀጠናው ላይ ሥራ እየሰራን ነው ያለነው " ሲሉ መልሰዋል።

አካባቢው ላይ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ያደርሳሉ፣ ለመሆኑ ጥቃቱን ለምን በቋሚነት ማስቆም አልተቻለም ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ " ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ " ብለዋል።

" ከዚህ በፊት በኛ ክልል ላይ የነበረው ችግር ይታወቃል፤ ችግሩን ለመፍታት ተሰርቶ ችግሮቹ መስመር ይዘዋል " ያሉት ኃላፊው " አሁን ቅርብ ጊዜ እያስቸገረን የሚገኘው ከፅንፈኛ 'ፋኖ' ጋር ተያይዞ የተሰራ ሥራ ነው። የፅንፈኛ 'ፋኖ' ተልዕኮ ነው ቀጠናችን ላይ እየበጠበጠ የሚገኘው፤ እሱ ላይ ደግሞ ተመጣጣኝ እርምጃዎችን እየወሰድን እንገኛለን " ብለዋል።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ "ፋኖ" እንቅስቃሴ አለ ወይ ? በሚል ለቀረበ ጥያቄ " ከዚህ በላይ የምሰጠው መግለጫ አይኖርም። የሰጠሁት መረጃ በቂ ነው " ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መስከረም 17 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች