ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#MoE

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#MoE
#MoE

ትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ግቢዎቻቸውን ከማንኛውም ወታደራዊና የትጥቅ እንቅስቃሴ ነፃ እንዲያደርጉ አስጠንቅቋል።

ሚኒስቴሩ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው ለመቐለ፣ አክሱም፣ ዓዲግራት እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች በጻፈው ደብዳቤ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲዎቹ ግቢ ውስጥ የሚገኙ የጦር ቁስለኞችና ታጣቂዎች እስካልወጡ ድረስ ተማሪዎችን እንደማይመድብ ገልጿል።

በትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተጻፈው ደብዳቤ፣ ቀደም ሲል በመቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ኩሓ ካምፓስ እና በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምውፃእ ወርቂ ካምፓስ የጦር ቁስለኞች መቀመጣቸውን ይጠቅሳል።

በቅርቡም በአክሱምና አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ዋና ግቢዎች ውስጥ የጦር ቁስለኞች መቀመጣቸው መረጋገጡን ደብዳቤው ይገልጻል።

ሚኒስቴሩ ይህ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሲቪልና ከትምህርታዊ ተልዕኳቸው ውጭ ለወታደራዊ ዓላማ እየዋሉ መሆናቸውን እንደሚያመለክት ገልጿል።

ይህም የተማሪዎችን ሕይወት፣ ደኅንነትና ሰላማዊ የመማር ሁኔታ ሊያሰጋ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ሚኒስቴሩ ለዩኒቨርሲቲዎቹ በዋናነት ሦስት መመሪያዎችን ሰጥቷል ፦

- በግቢዎቹ የሚገኙ የጦር ቁስለኞችን በአስቸኳይ ማስወጣት፤
- ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ግቢዎች ከማንኛውም ወታደራዊና የትጥቅ እንቅስቃሴ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ፤
- የዩኒቨርሲቲ ሀብቶች ለወታደራዊ ዓላማ እንዳይውሉ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ።

ይህ ቁጥጥር የዩኒቨርሲቲ ካምፓሶችን ብቻ ሳይሆን የተማሪዎች መኖሪያዎችን፣ የሕክምና ማዕከላትን፣ ሕንፃዎችን፣ መጋዘኖችንና ተሽከርካሪዎችንም እንደሚያካትት ተገልጿል።

የዩኒቨርሲቲዎቹ አመራሮችና ቦርዶችም መመሪያዎቹን በቅርበት እንዲከታተሉና አፈጻጸሙን እንዲያረጋግጡ ታዘዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲ ምደባ ሲያደርግ የተማሪዎችን ሕይወትና ደኅንነት፣ ሰላማዊ የመማር ሁኔታ እና የትምህርት ቀጣይነት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጿል።

በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ ግቢዎቹ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ መሆናቸው በአግባቡ ካልተረጋገጠ፣ ተማሪዎችን ወደእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች እንደማይመድብ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ውሳኔውም የተማሪዎች ደኅንነትና ሰላማዊ የመማር ሁኔታ እስኪረጋገጥ ድረስ ተፈጻሚ እንደሚሆን ገልጿል።

ከዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ ውጭ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን አለመመልከት ወይም ሪፖርት አለማድረግ ከፍተኛ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል አስጠንቅቋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የዩኒቨርሲቲ አመራር ደብዳቤው እንደደረሳቸው ለቢቢሲ አማርኛ አረጋግጠዋል።

ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲም ደብዳቤውን በፌስቡክ ገጹ ላይ አጋርቶ ከደቂቃዎች በኋላ ሰርዞታል።

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዱልቃድር ከድር በበኩላቸው ደብዳቤው እንዳልደረሳቸው ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፤ መቐለ ዩኒቨርሲቲ የነባር የቅድመ-ምረቃ መደበኛ ተማሪዎች የ2019 ትምህርት ዘመን ሪፖርት ማድረጊያ ቀናት መስከረም 09 እና 10/2019 ዓ.ም መሆኑን አሳውቋል።

በመሆኑም ነባር ተማሪዎች በተጠቀሱት ቀናት ሪፖርት እንዲያደርጉ ዩኒቨርሲቲው አሳስቧል።

ጳጉሜን 2 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች