ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" ህፃናት ልዩ ትኩረት ይሻሉ፤ ...ወላጆች ልጆቻችሁ የሚውሉበትንና የሚጫወቱበትን ቦታ ማወቅና መከታተል ይገባል " - ፖሊስ

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" ህፃናት ልዩ ትኩረት ይሻሉ፤ ...ወላጆች ልጆቻችሁ የሚውሉበትንና የሚጫወቱበትን ቦታ ማወቅና መከታተል ይገባል " - ፖሊስ
" ህፃናት ልዩ ትኩረት ይሻሉ፤ ...ወላጆች ልጆቻችሁ የሚውሉበትንና የሚጫወቱበትን ቦታ ማወቅና መከታተል ይገባል " - ፖሊስ

👉 " ሰራተኛ ስትቀጥሩ ጥንቃቄ አድርጉ ! "


ህፃን ፊዮና ሰለሞን ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ/ም ከምሽቱ 12፡30 ሠዓት አካባቢ ከቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ቦሌ ቡልቡላ በቤት ሰራተኛቸው የእገታ ወንጀል ተፈጽሞባት 3 ሚሊዮን ብር ከተጠየቀባት በኋላ አጋቿ ሰራተኛ ተይዛ ህጻኗ ወደ ቤተሰቦቿ እንድትመለስ ተደርጓል።

መቅደስ ሞገድ የተባለችው ተጠርጣሪ አቶ ሰለሞን ፈንታሁንና ወ/ሮ ሄለን ኃይለሚካሄል ቤት በቤት ሰራተኝነት ለሶስት ወራት ከሰራች በኋላ " ቤተሰብ ልጠይቅ " ብላ ፈቃድ ጠይቃ ከሄደች በኋላ ሳትመለስ ትቀራለች።

ከሁለት ወራት በኋላ ግን ከአንድ ግብረ አበሯ ጋር ወደ ቀድሞ አሰሪዎቿ አካባቢ በመመለስ ህፃን ፊዮና ሰለሞንን ከምትጫወትበት ቦታ ይዛ ትሰወራለች።

ከዚያም ግብረ አበሯ ለህፃኗ ቤተሰቦች በስልክ 3 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ይዝታል፤ ቤተሰቡ ዛቻውን በመፍራት 370 ሺህ ብር በባንክ ገቢ ያደርጋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በቴክኖሎጂ በመታገዝ ባደረገው ክትትል፣ ተጠርጣሪዋ ህፃኗን ይዛ ወደ አማራ ክልል መሄዷን ለይቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር ባደረገው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠርጣሪዋን ከጎንደር ከተማ ማራኪ ክ/ከተማ ዩኒቨርሲቲ ጫካ ውስጥ በጥቆማና ክትትል በቁጥጥር ስር ሊያውል ችሏል።

ታጋችዋ ህፃን ፊዮና ሰለሞን ትላንት ምሽት ላይ ከባህር ዳር አዲስ አበባ ገብታለች።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የታክቲክ ወንጀሎች ምርመራ ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አድማሱ ኢፋ፣ ህፃናት ልዩ ትኩረት ከሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ቀዳሚ በመሆናቸው መጠበቅ፣ መንከባከብና ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ወላጆች ልጆቻቸው የሚውሉበትንና የሚጫወቱበትን ቦታ ማወቅና መከታተል የሚገባ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የህፃን ፊዮና እናት ወ/ሮ ሄለን ኃ/ሚካኤል፥ ተጠርጣሪዋ መቅደስ ሞገስ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ስትሰራ የቆየች በመሆኑ ህጻኗ ስለምታውቃት አጋጣሚ ተጠቅማ የእገታ ወንጀሉን በመፈፀሟ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

በወቅቱ የልጃችንን መጥፋት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ካመለከትን ጀምሮ ፖሊስ ቀን ከሌሊት ፍለጋውን በማድረግ ልጃችንን በእጃችን በማስገባቱ ወደር የሌለው ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል። " በስራው ለተሳተፉ በሙሉ ክብር ይገባቸዋል " ሲሉ ገልጸዋል።

" ማንኛውም ዓይነት ወንጀል ፈፃሚዎች ለጊዜውም ቢሆን ከሰው ዓይንና ጆሮ ቢሰወሩም ከህግ ማምለጥ አይችሉም " ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በስራው ተሳታፊ ለነበሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና የጎንደር ከተማ ፖሊስ እንዲሁም ሌሎች የፀጥታ ተቋማት ላደረጉት ቀና ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

ህብረተሰቡ የቤት ሰራተኞችን ሲቀጥር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እንዲሁም በአካባቢው ላይ የሚያያቸውን ማንኛውም አጠራጣሪ ጉዳዮች ለአቅራቢያ ፖሊስ መረጃ በመስጠት የህግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ እንደሚገባም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

#AddisAbabaPolice
ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች