ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" መሬቱ ነው፣ ዝናቡ አቁሮ ነው፣ ጎርፉ ወደ ፍሳሽ መውረጃ ስላልገባ ነው፣ የኔ ችግር አይደለም፣ የመንገዶች ባለስልጣን ችግር ነው፣ ብሎ ማሳበብ ምክንያት አይሆንም፤ ከተጠያቂነት ነጻ አያደ…

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" መሬቱ ነው፣ ዝናቡ አቁሮ ነው፣ ጎርፉ ወደ ፍሳሽ መውረጃ ስላልገባ ነው፣ የኔ ችግር አይደለም፣ የመንገዶች ባለስልጣን ችግር ነው፣ ብሎ ማሳበብ ምክንያት አይሆንም፤ ከተጠያቂነት ነጻ አያደ…
" መሬቱ ነው፣ ዝናቡ አቁሮ ነው፣ ጎርፉ ወደ ፍሳሽ መውረጃ ስላልገባ ነው፣ የኔ ችግር አይደለም፣ የመንገዶች ባለስልጣን ችግር ነው፣ ብሎ ማሳበብ ምክንያት አይሆንም፤ ከተጠያቂነት ነጻ አያደርግም " - አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ

በክረምት ወቅት አሽከርካሪዎች መንገድ ላይ የተጠራቀመን የዝናብ ወይም የፍሳሽ ውሃ እግረኞች ላይ ረጭተው ሲያልፉ ማየት የተለመደ ነው።

ነገር ግን በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ ከአንቀጽ 820 ጀምሮ እና በተከታዮቹ እንዲሁም የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው የመንገድ የትራንስፖርት ደንብ ድርጊቱ በደንብ መተላለፍ ወንጀል ተቆጥሮ ከ3 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያ እና ጠበቃ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

የህግ ባለሙያው እና ጠበቃው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በዝርዝር ምን አሉ ?

" አንድ አሽከርካሪ መንገድ ላይ እያሽከረከረ በሚሄድበት ወቅት የእግርኞችን ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ ማሽከርከር እንዳለበት የመንገድ ደህንነት፣ የስነ-ስርዓት ደንብ እና የፌደራል የወንጀል ህግ በግልጽ ይደነግጋል።

በአሽከርካሪዎች እንደዚህ አይነት ጉዳት የሚደርሰው በቸልተኝነት ነው። በእግርኛው ላይ ላደረሰው ጉዳት በደረቅ ወንጀል (ታስቦበት በተፈጸመ ከባድ ወንጀል) ሳይሆን በቸልተኝነት በፍጸመው የደንብ መተላለፍ ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል።

እንደዚህ አይነት ወንጀል ሰርተው በፍርድ ቤት ክስ ቀርቦባቸው ጥፋተኛ ከተባሉ በደንብ መተላለፍ ወንጀሎች በመደበኛው የወንጀል ህግ ሶስት አመት በማይበልጥ ቀላል እሰራት ወይም በአማራጭ በገንዘብ መቀጮ ይቀጣሉ።

ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ጉዳት የደረሰበት አካል የተሽከርካሪውን የሰሌዳ ቁጥር ይዞ ለፖሊስ አመልክቶ ከሆነ እና በአሽከርካሪው ቸልተኝነት ምክንያት የተጠራቀመው ውሃ በሰውየው ላይ ተረጭቶ እንዳበላሸው በምስክር ማረጋገጥ ሲችል ነው።

የዝናብ ውሃም ይሁን ሌላ ማንኛውም ፈሳሽ በተጠራቀመበት ቦታ ላይ አሽከርካሪው እግረኛውን ቀስ ብሎ ማሳለፍ እና በዝግታ ማሽከርከር ሲገባው  ተሽከርካሪው በመጣበት ፍጥነት ግለሰቡን ረጭቶት ከሄደ ተጠያቂ ነው። እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲፈጠሩ አሽከርካሪው በረጨበት አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ማመልከት ይጠበቃል።

በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ ከአንቀጽ 820 ጀምሮ እና በተከታዮቹ ደንብ መተላለፍን በተመለከተ የወጡ የወንጀል ተጠያቂነት ድንጋጌዎች አሉ።

ሌላው የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው የመንገድ ትራንስፖርት ደንብ አሽከርካሪዎች የመንገድ ደህንነትን ባከበረ፣ በተጠበቀ ሁኔታ ማሽከርከር እንዳለባቸው እና በቸልተኝነት ለሚፈጽሙት ማንኛውም ወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስቀምጧል።

በተጨማሪም በስልክ እና በላፕቶፕ ላይ ጉዳት ካደረሰ በፍትሐ ብሔር ሁሉ መክሰስ ይቻላል። ግን ምስክሮች ያስፈልጋሉ። በቸልተኝነት ለደረሰ ጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው የፍትሐብሔር ህጉም በግልጽ አስቀምጧል። 

በክረምት ወቅት በከፍተኛ የዝናብ መጠን አስፋልቶች ላይ ውሃ ሊከማች ይችላል፣ ውሃ የራሱ የፍሰት ስርዓት ስላለው በአንድ ጊዜ ወደ ፍሳሽ መውረጃ ላይ ላይገባ ይችላል። አሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ለእግርኞች ቅድሚያ የሰጠ፣ እግርኞችን ያከበረ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በውሃ እና በመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ እግረኛን ረጭተው ቢሄዱ በፈጸሙት የቸልተኝነት ጥፋት በህግ ይጠየቃሉ። የሞራል ኃላፊነትም እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው።

አሽከርካሪዎች ደረጃውን እና ምቾቱን በተጠበቀ ተሽከርካሪ ውስጥ ሆነው ሲሄዱ የእግርኛውን እንቅስቃሴ እና ሁኔታ ደግሞ ያከበረ፣ የጠበቀ እንቅስቃሴ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

' መሬቱ ነው፣ ዝናቡ አቁሮ ነው፣ ጎርፉ ወደ ፍሳሽ መውረጃ ስላልገባ ነው፣ የኔ ችግር አይደለም፣ የመንገዶች ባለስልጣን ችግር ነው ' ብሎ ማሳበብ ምክንያት አይሆንም፤ ከተጠያቂነት ነጻ አያደርግም።

እንደዚህ አይነት ጥፋት የሰራ ተሽከርካሪ የሰሌዳ ቁጥሩ እስከተያዘ ድረስ ተጠያቂ ነው።

አሽከርካሪው ድርጊቱን ቢክድ እንኳ ተጠያቂ ለማድረግ የተበደለው አካል የተሽከርካሪውን የሰሌዳ ቁጥር ይዞ ለፖሊስ ማመልከት እና ሁኔታውን በቅርበት ያየ የአይን ምስክር ማቅረብ ይኖርበታል።

ድርጊቱን የተመለከቱ ሰዎችም የምስክርነት ቃል መስጠታቸው ግለሰቡን እንደ መተባበር ሳይሆን የፍትህ ስርዓቱን እንደ ማገዝ የሚቆጠር በመሆኑ፣ ምስክርነታቸውን መስጠት አለባቸው።

አሽከርካሪዎች እንደዚህ አይነት ነገሮች በህግ ተጠያቂነትን እንደሚያመጡ አውቀው ህጉን አክብረው ሊንቀሳቀሱ ይገባል። "

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ነሐሴ 26 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች