ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

"ሽዓይነስውራን ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማለፊያ ውጤት ብናመጣም የዩኒቨርሲቲ ምደባ ማወቅ አልቻልንም " - ተማሪዎች

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
"ሽዓይነስውራን ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማለፊያ ውጤት ብናመጣም የዩኒቨርሲቲ ምደባ ማወቅ አልቻልንም " - ተማሪዎች
"ሽዓይነስውራን ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማለፊያ ውጤት ብናመጣም የዩኒቨርሲቲ ምደባ ማወቅ አልቻልንም " - ተማሪዎች

👉 " ቅሬታ ማቅረቢያ አለ፤ እዚያ ላይ 'ዓይነስውር ነኝ ግን አልተመደብኩም' ብለው ያስገቡ " - ትምህርት ሚኒስቴር

ዘንድሮ የ12 ክፍል ፈተና ወስደው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ያመጡ ዓይነውራን ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ ከሞላን በኋላ ምደባ ማወቅ አልቻልንም የሚል ቅሬታ በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል አቅርበዋል።

ተማሪዎቹ በሰጡን ቃል ምን አሉ ?

አንደኛው ተማሪ፣ "በዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ወስጄ ከዓይነስውራን ማለፊው 250 ነጥብ በላይ 288 ውጤት አምጥቻለሁ። ዓይነስውራን 5 የትምህርት አይነቶችን ከ500 ስለሆነ የተፈተነው ማለፊ ነጥቡ 250 እና ከዚያ በላይ ነው።

ነገር ግን ዩኒቨርሲቲ ምደባ ማወቅ አልቻልንም። ለማየት ስንሞክር 'Replacement view currently closed' እያለ ሲስተሙ አይሰራም። ሲስተሙ እንዲህ የሆነብን ከ250 እስከ 299 ማለፊያ ውጤት ላመጣነው ብቻ ነው።

ዓይነስውራን ላልሆኑትም ሆነ ዓይነስውራን ሆነው ከ300 በላይ ያመጡት ሊንኩን ከፍተው ዩኒቨርሲቲ ምደባ ማወቅ ችለዋል። እኛ ማየት አልቻልንም፤ የት ዩኒቨርሲቲ ሄደን መማር እንዳለብን አላወቅንም፤ ግራ ገብቶናል" ብሏል።

ሌላኛው ተፈታኝ፣ "የ12ኛ ክፍል የዘንድሮ ተፈታኝ ነኝ። ከ500 298 ማለፊያ ውጤት አምጥቻለሁ። ነገር ግን ሌሎችንም ጨምሮ ማለፊያ ውጤት ያመጣን ዓይነስውራን የዩኒቨርሲቲ ምደባ ለማወቅ ሲስተሙ አላስተናገደንም።

ከነሐሴ 28/2018 ዓ/ም እስከ ጳጉሜ መጨረሻ ነበር የዩኒቨርሲቲ ምደባ ለመሙላት ቀነ ገደብ የተሰጠን፤ ሲስተሙ ዩኒቨርሲቲ መምረጥ እንደምንችል አሳይቶን መረጥን፤ በኋላ ምደባ ለመሙላት የ5 ቀናት ጊዜ ገደብ ተጨመረ፤ ለምን ተጨመረ ብለን ሊንኩን ከፍተን ስናይ 'Summit' ብለን ልከን የነበረውን እንዳላመለከትን ነው ሲስተሙ ያሳየን።

ከ300 በላይ ውጤት ያመጡትን ዓይነስውራን ግን ሲስተሙ አስተናግዷቸዋል። 250 እና ከዚያ በላይ ማለፊያ ውጤት ማምጣት ስለሆነ የሚጠበቅብን እሱን አምጥተናል፤ ምደባ ግን አላየንም" ብሏል።

ሌላኛዋ ተፈታኝ፣ "ዓይነስውር ተማሪ ነኝ፤ ዩኒቨርሲቲ ምደባ ሞልቼ ነበር ነገር ግን አልተመደብኩም። ውጤቴ ለማለፊያ በቂ ነው። እንዳንጠብቅ ተማሪ እየጠሩ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፤ ግራ ተጋባን" ስትል ገልጻለች።

ሌሎች ሁለት ተማሪዎችም ተመሳሳይ ቅሬታ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የተናገሩ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ትምህርት ሚኒስቴር በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ምን መለሰ ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለተማሪዎቹ ቅሬታ ምላሽ የጠየቃቸው የትምህርት ሚኒስትር ዴዔታ ክንደያ ገ/ህይወት (ፕ/ር) ምላሽ ሰጥተዋል።

"በምደባው ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎች ቅሬታቸውን ለዚሁ ሲባል በተዘጋጀው የኦንላይን ሥርዓት ብቻ ይህ ምደባ ይፋ ከሆነበት ቀን ጀምሮ በ5 ቀናት ውስጥ አስፈላጊውን መረጃና ማስረጃ በማያያዝ እንዲያቀርቡ እናሳስባለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የዘርፉን አካላት፣ "ቼክ አድርጉ ብያቸው ቼክ ተደርጓል። ዳታ ከፈተናዎች ኤጀንሲ ነው ወደኛ የሚመጣው። አድሚሽናቸው ላይ ብላይንድ (Blind) የሚል ምርጫ ካላስገቡ ዓይነስውራን ባልሆነ ሊታዩ ይችላሉ።

አንዳንዴ ዓይነስውር ሆነውም እያሉ ዓይነስውር ያልሆኑ አድርገው ሊልኩት ይችላሉ። እንደዛ ሲሆን ፊልተር ይሆናል።  ዓይነስውራን ሆነው የተመደቡ አሉ። ግን ደግሞ በግል የጠየቁ ሰዎች ቅሬታ ማቅረቢያ አለ፤ እዚያ ላይ 'ዓይነስውር ነኝ ግን አልተመደቤኩም' ብለው ያስገቡ። ቅሬታቸው ይስተናገዳል" ብለዋል።

ከአንድ ቀን በፊት ይፋ በሆነውና አምስት ቀናት ቀነ ገደብ በተቀመለጠት የቅሬታ ማመልከቻ ሊንክ በቡድን ሳይሆን በግል እንዲያመለክቱም አሳስበዋል።

የቅሬታ ማቅረቢያ ሊንኩ፥ https://student.ethernet.edu.et/complaints መሆኑን ልከዋል።

#ማሳሰቢያ፥ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በአካል በመሄድ የሚቀርብ የምደባ ቅሬታ የማይስተናገድ መሆኑን ተማሪዎች እና ወላጆች እንዲገነዘቡ ተጠይቋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
መስከረም 7 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች