ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#ችሎት

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#ችሎት
#ችሎት

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሃላፊዎች ተፈጽሟል በተባለ የሰነድ ማጭበርበር እና የሙስና ወንጀል ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ፖሊስ 11 ቀናት ተፈቀደለት።

👉 በምርመራ ላይ በሚገኘው የወንጀል መዝገብ ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በሃሰተኛ ቪዛ ከ 30 ሺ በላይ ሰራተኞችን ወደ ጆርዳን በመላክ ተጠርጥረዋል።

👉 በእዚህም ህገወጥ ድርጊት በሁለት ሃሰተኛ የባንክ አካውንቶች ከ 200 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ሰብስበዋል በሚል በፖሊስ ምርመራ እየተከናወነባቸው ይገኛል።


(ቲክቫህ ኢትዮጵያ)

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ገበያ መረጃ (ELMIS) ክፍል ኃላፊ እና የውጭ ሀገር ሥራ ማሰማራት ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ በጠቅላላው በ18 ተጠርጣሪዎች ላይ የተጀመረው የከፍተኛ ሙስና እና የሰነድ ማጭበርበር ወንጀል ምርመራ በችሎት ላይ ይገኛል።

በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች:-

1ኛ አቶ ብርሃኑ አለቃ አስገዶም (የELMIS ክፍል ኃላፊ)፣

2ኛ አቶ ኤርሚያስ ተክሉ ዘነበ (የውጭ ሀገር ሥራ ማስማማትና ፈቃድ አሰጣጥ ሥራ አስፈጻሚ)፣

3ኛ ነቢል አንዋር፣

4ኛ ማቴዎስ ማሙዬ፣

5ኛ ቢኒያም ሙሰማ

6ኛ ኢክራም አማን እና ሌሎችም ሲሆኑ፤ በጠቅላላው በመዝገቡ 18 ተጠርጣሪዎች ተካተዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 8ቱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች፣ 2ቱ የኤጀንሲ ተወካዮች እና ቀሪዎቹ 8ቱ ደግሞ ሕገ-ወጥ ድርጊቱን ሲያቀላጥፉ የነበሩ አገናኞች (ደላላዎች) መሆናቸውን ፖሊስ ያጠናከረው መዝገብ ያስረዳል።

ተጠርጣሪዎቹ ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።

ፖሊስ ከእዚህ ቀደም ለችሎቱ ባቀረበው ያልተጠናቀቀ የምርመራ መዝገብ ላይ ተጠርጣሪዎቹ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀምና የሲስተም ብልሽት በመፍጠር ተከታታይ የሙስና ወንጀሎችን መፈጸማቸውን ገልጿል።

1ኛ ተጠርጣሪ አቶ ብርሃኑ አለቃ የELMIS (የሥራ ገበያ መረጃ) ሲስተምን ብቻቸውን በመቆጣጠር፣ ኦንላይን ሲስተሙ እንዳይሠራ በማድረግና ማስታወቂያዎች ከሲስተሙ ላይ እንዲሰረዙ በማድረግ ኤጀንሲዎችና ግለሰቦች ለሕገ-ወጥ ድርድር እንዲገደዱ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ዜጎች ተገቢውን ሥልጠና ሳይወስዱና የCOC ፈተና ሳይቀመጡ እንዳለፉ በማስመሰል፣ ለእያንዳንዱ ሰው እስከ 25 ሺህ ብር በመቀበል ሐሰተኛ የብቃት ማረጋገጫ እና የሠራተኞች ውል በማዘጋጀት ወደ ውጭ እንዲወጡ አድርገዋል ተብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ የጥፋት ድርሻቸው በምርመራ የሚረጋገጥ ቢሆንም በዚህ መልኩ በ6 ወራት ውስጥ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች በሐሰተኛ ቪዛ ወደ ጆርዳን እንዲላኩ ማደረጋቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ሕጋዊ የሆኑ ኤጀንሲዎችን ያለምንም ጥፋት በማገድና እገዳውን ለማንሳት በአጠቃላይ እስከ 10 ሚሊዮን ብር ድረስ እንዲከፍሉ መጠየቃቸው በፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ ተመላክቷል።

በአንጻሩ ከሀገራት ጋር ስምምነት የሌላቸውን 5 ኤጀንሲዎች በገንዘብ ድርድር ሕጋዊ ሽፋን እንዲያገኙ ሲያደርጉ መቆየታቸውም እንዲሁ።

ሐሰተኛ የሰራተኛ ሪፖርቶችን በማዘጋጀት ሀገሪቱ ማግኘት የነበረባትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲታጣ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል።

ፖሊስ ባደረገው ኦዲትና ክትትል፣ በተከሳሾቹ ስም በተከፈቱ ሁለት ሐሰተኛ የባንክ አካውንቶች ውስጥ የነበረ 261 ሚሊዮን ብር እንዲታገድ አድርጓል።

በተጨማሪም በተጠርጣሪዎቹ፣ በቤተሰቦቻቸውና በጓደኞቻቸው ስም የሚገኙ፦

• 6 የመኖሪያ ቤቶች፣ እና
• 4 ተሽከርካሪዎች እንዲታገዱ ማድረጉን አብራርቷል።

በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት ፌደራል ፖሊስ የሲስተም እና የአሰራር ኦዲት ለማድረግ፣ እንዲሁም ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የጠየቀ ቢሆንም፣ ችሎቱ መዝገቡን ከመረመረ በኋላ ፖሊስ ካቀረበው ጥያቄ ላይ 3 ቀናትን በመቀነስ ከነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የሚታሰብ የ11 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

የፖሊስን የተጠናከረ የምርመራ መዝገብ ለመስማት ችሎቱ ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚሰየም ይሆናል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች