ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

"ህንፃው ነው የተጎዳው። ከህንፃው ሦስተኛው ጣራ ተቃጥሏል፤ መስኮቶቹ ተጎድተዋል" - ዩኒቨርሲቲው

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
"ህንፃው ነው የተጎዳው። ከህንፃው ሦስተኛው ጣራ ተቃጥሏል፤ መስኮቶቹ ተጎድተዋል" - ዩኒቨርሲቲው
"ህንፃው ነው የተጎዳው። ከህንፃው ሦስተኛው ጣራ ተቃጥሏል፤ መስኮቶቹ ተጎድተዋል" - ዩኒቨርሲቲው

በዛሬው እለት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ባለ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ህንጻ ላይ የተሰተውን የእሳት አደጋ በተመለከተ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የዩኒቨርሲቲውን አካላት ማብራሪያ ጠይቋል።

በዚህም፣ አደጋው የተነሳው በርካታ ቢሮዎች ባሉበት ህንፃ መሆኑ ታውቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጉቼ ጉሌ (ዶ/ር) በሰጡን ቃል፣ "በመንገድ ላይ ሆኘ ሁኔታውን እየተከታተልኩ ነበር። እሳቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን ደውዬ አረጋግጫለሁ። ብዙ ነገር አልተጎዳም። ብዙ ጉዳት አልደረሰም" ብለዋል።

የእሳት አደጋው የተነሳው የህንፃ መጨረሻ ፍሎር ላይ ባለ አንድ ክፍል መነሳቱን የነገሩን ፕሬዚዳንቱ፣ "ኮንታክት ተፈጥሮ ነው አደጋው የተፈጠረው። ወደታኞቹ የህንፃው ፍሎሮች አልወረደም። የላኞቹንም በአቅራቢ ያሉትን እንጅ ብዙ አልጎዳም" ሲሉም አክለዋል።

የእሳት አደጋው የተነሳው "ቤተመፅሐፍት" ላይ ነው የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጩ የተስተዋሉ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ አደጋው የተነሳው "ላይብረሪ ላይ አይደለም፤ ቢሮዎች ያሉበት ህንፃ ላይ ነው። መማሪያ ክፍሎችም ከስር አሉ" በማለት  ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አደጋው የተነሳው በማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ቢሮዎች መሆኑን ገልጸው፣ "እሳቱ  የሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ውሏል። ብዙ የከፋ ጉዳት አልደረሰም" ሲሉ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ገደማ ነግረውናል።

ሌላኛው ስሜ አይጠቀስ ያሉ የዩኒቨርሲቲው አመራር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ በአንድ ህንፃ መጨረሻ ላይ በሚገኝ ክፍል የእሳት እደጋ መከሰቱን ገልጸው፣ "አሁን ግን የዞኑ መንግስት፣ የከተማው አስተዳደር ተረባብበው ተቆጥጥረውታል" ብለዋል።

በአደጋው የደረሰው የጉዳት መጠን ሲጠየቁ፣ "ያን ያክል ጉዳት አልደረሰም፤ ህንፃው ነው የተጎዳው። ከህንፃው ሦስተኛው ጣራ ተቃጥሏል፤ መስኮቶቹ ተጎድተዋል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አደጋው የደረሰበት ህንፃ ቢሮ ጭምር መሆኑ ተገልጿል፤ ውስጥ ንብረት አልነበረውም? ተብሎ ሲጠየቁ፣ "ንብረት ነበረ ወጥቷል። እሳቱ ጣሪያውን ስለያዘ ከውስጥ ያሉ ንብረቶች ሁሉ ወጥተዋል። ንብረት ላይ ያን ያክል የደረሰ ጉዳት የለም፤ ህንፃው ነው ትንሽ የተጎዳው" ብለዋል።

መንስኤውን የጠየቅናቸው አመራሩ፣ "መንስኤው ለጊዜው አይታወቅም፤ በአቅራቢያ የነበሩ ሰዎች ግን 'የኤሌክትሪክ ኮንታክት ነው' እያሉ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል። የእሳት አደጋው የተነሳው ዛሬ ጠዋት 4 ሰዓት ገደማ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው አመራር፣ "የተቃጠለው ህንፃ ማህበራዊ ሳይንስ ክላስተር ህንፃ ነው። በህንፃው መማሪያ ክፍሎች፣ ቢሮዎች (የፋይናስ ቢሮ፣ የሰው ሀብት ቢሮ) አሉ፤ የዲፓርትመቶች ቢሮዎች (የእንግሊዝኛ ዲፓርትመንት፣ ወላይትኛ ዲፓርትመንት) እና ሌሎችም አሉ። የGIS ላብራቶሪ፤ የቋንቋ ላብሪቶሪም አሉ" በማለት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

#ጥንቃቄ ፦ በማህበራዊ ሚዲያዎች " ዩኒቨርስቲው ሙሉ በሙሉ እየተቃጠለ ነው " በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍጹም ሀሰተኛ ነው።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች