ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

በሲዳማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ 3 ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ።

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
በሲዳማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ 3 ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ።
በሲዳማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ 3 ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ።

በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን፣ ዳሌ ወረዳ ዋራ ቀበሌ ጋላማ በተባለ አካባቢ ትናንት ምሽት 2 ሰዓት ገደማ በደረሰ ከባድ የትራፊክ አደጋ 3 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 4 ሰዎች መጎዳታቸውንና 11 ተሽከርካሪዎች መጎዳታቸውን የክልሉ ፖሊስ ገልጿል።

የክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የመንገድ ደህንነትና ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መለሰ ቡኑራ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደገለጹት፣ አደጋው የተከሰተው ተሳፋሪዎችን ጭኖ ከሀዋሳ ወደ አለታ ወንዶ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2-03698 ሲዳ የሆነ ዶልፊን ተሽከርካሪ፣ ከአለታ ወንዶ ወደ ሀዋሳ ይጓዝ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-50656 የሆነ FSR ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ነው።

በመጀመሪያው ግጭት አንድ ሰው ሕይወቱን ወዲያውኑ ሲያጣ፣ ተከታትለው ይጓዙ የነበሩ ሌሎች ተሽከርካሪዎች በአደጋው ሥፍራ ቆመዋል። ተሳፋሪዎችም ከተሽከርካሪዎቻቸው ወርደው የአደጋውን ሁኔታ ሲመለከቱ ነበር።

በዚህ ወቅት ከሀዋሳ ወደ አለታ ወንዶ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኢት ኮድ 3A-41656 የሆነ ሲኖትራክ ተሽከርካሪ ወደ አደጋው ሥፍራ በመድረስ በዚያ ተደርድረው ቆመው በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ አልፏል።

ከዚያም ሲኖትራኩ በሌላ አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በመውደቁ 2 ሰዎች በቦታው ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 2 ሰዎች ከባድ እና 2 ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በአጠቃላይ በዚህ አደጋ 3 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 4 ሰዎች ቆስለዋል፤ በ11 ተሽከርካሪዎችም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

ዋና ኢንስፔክተር መለሰ እንደገለጹት፣ አደጋው የደረሰው በምሽት መሆኑ፣ በወቅቱ የነበረው ዝናባማ ሁኔታ እና ሲኖትራኩ በከፍተኛ ፍጥነት መጓዙ የአደጋውን አደገኛነት አባብሶታል። እነዚህ ሁኔታዎች ታሳቢ ሲደረጉ አደጋው ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበር ጠቁመዋል።

በመሆኑም አሽከርካሪዎች በተለይም በክረምትና ዝናባማ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ የተሽከርካሪ ፍጥነትን እንዲቀንሱ እና ከምሽት ጉዞ በተቻለ መጠን እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
ነሐሴ 10 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች