ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎች አፍሪካን ወክለው ለዓለም አቀፍ የምስለ-ችሎት ፍጻሜ አለፉ።

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎች አፍሪካን ወክለው ለዓለም አቀፍ የምስለ-ችሎት ፍጻሜ አለፉ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎች አፍሪካን ወክለው ለዓለም አቀፍ የምስለ-ችሎት ፍጻሜ አለፉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪዎች በአህጉራዊው የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ህግ እና የግልግል ዳኝነት (arbitration) የምስለ-ችሎት ውድድር (FDI Moot) የዞኑ አሸናፊ በመሆን አፍሪካን ወክለው ለዓለም አቀፉ ፍጻሜ ማለፋቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፉበት በዚህ ፈታኝ ውድድር ከናይጄሪያ፣ ከኬንያ እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ 14 ቡድኖችን በመበለጥ ከሰብ-ሳሃራን አፍሪካ አንደኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል።

በዚህ ውድድር ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ወክለው የተሳተፉት ፦

ባምላክስራ ፋሲል (የ3ኛ ዓመት የህግ ተማሪ)
ቃልኪዳን ሰብስቤ (የ4ኛ ዓመት የህግ ተማሪ)
ዲቦራ ታደሰ (የ4ኛ ዓመት የህግ ተማሪ) እና
ናሆት ግርማ (የ5ኛ ዓመት የህግ ተማሪ) ናቸው።

ለዚህ አህጉራዊ ውጤት ያበቃቸው ዋና ምክንያት ምንድን ነው ?

" ለዚህ ውጤት ያበቃን ቀደም ሲል በቪስ ሙት (Vis Moot) የነበረን ልምድ ነው። ከቡድናችን አራት አባላት መካከል ሦስቱ በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ውድድር ላይ ለአንድ አመት ተወዳድረዋል። ይህ ልምድ በጣም ጠቅሞናል።

አሁን ላይ የተወዳደርንበት ጉዳይ ከአለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ህግ እና የግልግል ዳኝነት ጋር የተያያዙ ውስብስብ ጥያቄዎችን ያካተተ ነበር።

ከዋና ዋናዎቹ የስነ-ስርዓት ክርክሮች መካከል ከሳሹ ቀደም ሲል አቤቱታውን ለሌላ አካል አቅርቦ ስለነበር አሁን እንዳይከለከል የሚለው እና የክስ ማገጃ ትእዛዝ መሰጠት አለበት ወይ ? የሚሉት ይገኙበታል።

የፍሬ-ነገር ክርክሩ በበኩሉ ፍትሃዊ እና እኩል እንክብካቤ እንዲሁም ንብረት መውረስን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን አካቷል።

በውድድሩ ወቅት የገጠመን ትልቁ ፈተና ከዳኞቹ ለሚቀርቡ ዝርዝር እና ያልተጠበቁ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ነው " ብለዋል።

የተወዳዳሪዎቹ መሪ የሆኑትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የህግ ተማሪ፣ የህግ ባለሙያ ቦርጋ ደለሳ፥ ተማሪዎቹ እስካሁን ያለምንም ድጋፍ ለዚህ ድል የበቁ ቢሆንም፣ በመጪው ኦክቶበር (October) ወር በቻይና በሚካሄደው የመጨረሻ ፍጻሜ ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ የገንዘብ እና የተቋማት ድጋፍ ይፈልጋሉ ብለዋል።

በተለይም ፦
- ለዓለም አቀፍ ጉዞ፣
- ለእንግዳ ማረፊያ፣
- ለቪዛ፣
- ከምዝገባ ጋር የተያያዙ ወጪዎች እና ለዝግጅት ድጋፍ የሚያስፈልግ በመሆኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት (በተለይም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን) የሕግ እና የንግዱ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች ትብብር እንዲያደርጉላቸውና እውቅና እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።

ይህ እድል የነዚህ አራት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን፣ ኢትዮጵያን እና የአፍሪካን የሕግ ትምህርት በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስተዋወቅና ለመወከል የሚሰጥ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።

ተወዳዳሪዎቹን ማግኘት የምትፈልጉ፣ የቡድኑ መሪ የሆኑትን የህግ ባለሙያ ቦርጋ ደለሳን በስልክ ቁጥር  +251925494142 ማግኘት ትችላላችሁ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ነሐሴ 6 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች