ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

ኤአይ (AI)ን እንዴት እንጠቀም ?

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
ኤአይ (AI)ን እንዴት እንጠቀም ?
ኤአይ (AI)ን እንዴት እንጠቀም ?

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ለረጅም ጊዜ እና ያለገደብ መጠቀም የሰዎችን የፈጠራ ብቃት እና ነገሮችን በጥልቀት የመመርመና የማሰብ ክህሎትን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል በቅርቡ የወጡ ተከታታይ ጥናቶች አመልክተዋል።

​በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች መረጃዎችን እና ውሳኔዎችን ሙሉ በሙሉ በኤአይ (AI) ላይ ጥገኞች ሆነው ማከናወን ሲጀምሩ " ኮግኒቲቭ ሰረንደር " ወይም የአእምሮን የማሰብ ስራ ለቴክኖሎጂ አሳልፎ የመስጠት ዝንባሌ ይታይባቸዋል።

ይህም አእምሮ በራሱ ጥረት መረጃዎችን የማቀናበር፣ የመተንተን እና አዳዲስ ሀሳቦችን የማመንጨት የተፈጥሮ ብቃቱ እንዲደክም ያደርገዋል።

በተለይ #ወጣቶች እና #ተማሪዎች ለተወሳሰቡ ጥያቄዎች እና ስራዎች ፈጣን ምላሽ ከኤአይ ማግኘት መልመዳቸው የራሳቸውን የአእምሮ አቅም የመጠቀም ተነሳሽነታቸውን እንደሚቀንሰው ተመራማሪዎች ያስጠነቅቃሉ።

ነገር ግን ቴክኖሎጂውን እየተጠቀሙ አእምሮን ሁል ጊዜ ንቁ፣ ብቁ እና ጤናማ አድርጎ ለማቆየት የሚረዱ በርካታ ሳይንሳዊ መንገዶች እንዳሉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

የአእምሮን የአስተሳሰብ ብቃት ላለማጣት ምን አይነት ልምዶች ማዳበር ይቻላል ?

- ከኤአይ (AI) የተገኙ ምላሾችን ወይም መረጃዎችን በቀጥታ ወስዶ ከመገልበጥ ይልቅ " ይህ መረጃ ትክክል ነው ? ምን ጎደለው ? አመክንዮአዊ ነው ? " በማለት በራስ አእምሮ መርምሮ፣ መዝኖ መጠቀም።

- ማንኛውንም ስራ፣ ጽሑፍ ወይም ፕሮጀክት ከመጀመርዎ በፊት መነሻ ሀሳቦችን እና እቅዶችን በራስ አእምሮ ማመንጨት እና ማስታወሻ መያዝ። ኤአይ ስራውን ለማስጀመር ሳይሆን የተጀመረውን ስራ ለማደራጀት ወይም ለመፈተሽ ብቻ መጠቀም።

- የፈጠራ እና የጥልቅ አስተሳሰብን የሚያነቃቁ እንደ መጽሐፍ ማንበብ፣ ስልታዊ ጨዋታዎችን መጫወት እና አዳዲስ ክህሎቶችን ያለ ቴክኖሎጂ እገዛ ለመማር መሞከር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መረጃዎች/ስራዎችን ለኤአይ ሰጥቶ ያለ ምንም ምርመራ፣ ማስተካከያና ደጋግሞ የማንበብ ጥረት በቀጥታ #በመገልበጥ አንዳንዴም እንደራስ ስራ ማስመሰል እየተለመደ መጥቷል። ይህ በጥልቀት ሳያስቡና ሳይመራመሩ በቴክኖሎጂ ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ መሆን አእምሮን የማሰብ ስራውን እንዲተው በማድረግ፣ እውነታን የመተንተን እና የጥልቅ አስተሳሰብ ብቃትን በከፍተኛ ደረጃ እየገደለው ይገኛል ፤ ሰዎች ትንሽ ስራ እንኳን ለመስራት የማይፈልጉ ስልቹና ሰነፍ እያደረጋቸውም ነው።

ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ኤአይ (AI) የሰውን ልጅ ሙሉ በሙሉ የሚተካ ሳይሆን እንደ ረዳት መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል የሚገባው ነው። ጥቅም የሚኖረውም የሰው ልጅ የራሱን የአስተሳሰብ ልዕልና ጠብቆ ሲቀጥል ብቻ ነው።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
#TikvahEthiopiaFamily

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች