ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" ዛሬ በእጃችን ገብቷል " ፤ " ልግደልልሽ ታዲያ ? " ... የመጨረሻው የስልክ ጥሪ

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" ዛሬ በእጃችን ገብቷል " ፤ " ልግደልልሽ ታዲያ ? " ... የመጨረሻው የስልክ ጥሪ
" ዛሬ በእጃችን ገብቷል " ፤ " ልግደልልሽ ታዲያ ? " ... የመጨረሻው የስልክ ጥሪ

በምዕራብ ወለጋ ገንጂ ወረዳ በሚገኘው የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት በታጣቂዎች ተፈጸመ በተባለ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። ከተገደሉት መካከል አቶ ዳንኤል ቀልቤሳ አንዱ ናቸው።

አቶ ዳንኤል ለዘጠኝ ዓመታት በወርቅ ማዕድን ልማት ፕሮጀክቱ ውስጥ ሰርተዋል።

ከዚህ በፊትም በኦሮሚያ የውሃ፣ የማዕድንና የኢነርጂ ቢሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ማገልገላቸውን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።

አቶ ዳንኤል በየጊዜው ለቤተሰቦቻቸው ይደውሉ ነበር።

በጥቃቱ ዕለት ግን ከጠዋት ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው ቢደውሉላቸውም ሊያገኟቸው አልቻሉም።

ከሰዓት በኋላ 9፡30 አካባቢ ግን በአቶ ዳንኤል ስልክ ተደወለ። የደወሉት ግን አቶ ዳንኤል አልነበሩም።

የቤተሰቡ አባል ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በአቶ ዳንኤል ስልክ የደወለው ሰው መጀመሪያ ስልኩ የአቶ ዳንኤል መሆኑን አረጋገጠ።

" የሆነ ሰው ' ሄሎ ' አለኝ… ' ይህ ስልክ የዳንኤል አይደለም ? ' ሲለኝ አዎ፣ የዳንኤል ነው አልኩት። 'ዳንኤል፣ ምንሽ ነው ? ' ብሎ ጠየቀኝ። "

ከዚያ የሰውየው ጥያቄ ወደ አቶ ዳንኤል ማንነትና ሥራ ተለወጠ።

" ' ዛሬ በእጃችን ገብቷል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ታውቂያለሽ ወይ ? ' ብሎ ጠየቀኝ። ' ካቢኔ ነው አይደል ? ' አለኝ። አይ፣ ዳንኤል ካቢኔ አይደለም። ከማኅበረሰቡ ጋር ነው የሚሠራው ስል መለስኩለት። "


ቤተሰቡ አቶ ዳንኤል የወርቅ ማውጫ ኩባንያ ውስጥ እንደሚሠሩ ነገሩት።
ሰውየው ግን ጥያቄውን ቀጠለ።

" ወርቅ ማውጫ ኩባንያ እንደሚሠራ ነገርኩት። ይህንን ከማለቴ በፊት ግን 'እያወቅሽ ነው አይደል የላክሽው' አለኝ፤ ምንድን ነው ? ይህ እኮ (በወርቅ ማውጫው ውስጥ መሥራት) ለዳንኤል አዲስ ነገር አይደለም ' በማለት አስረዳሁት። "


ከዚያ ጥያቄው ወደ ፖለቲካ ሥራ መለወጡን የቤተሰቡ አባል ያስታውሳሉ።

" 'የፖለቲካ ሥራ ነው አይደል የሚሠራው?' ሲለኝ በሙያው እንደሚሠራ ነገርኩት። ከዚያ 'ልግደልልሽ ታዲያ?' አለኝ። ከዚያ ቀጥሎ ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቀኝ።"

ቤተሰቡ እንደሚሉት በዚያ ሰዓት ከደወለው ሰው ጋር በጥንቃቄ መነጋገር መርጠዋል።

" እኔም ቀስ እያልኩ መለስኩለት፤ ከገደልከው ታሪክ ተጠያቂ ያደርግሃል፣ እግዚአብሔርም ይጠይቅሃል አልኩት። "


ከዚህ በኋላ ቤተሰቡ የአቶ ዳንኤልን ድምጽ እንዲያሰማቸው በተደጋጋሚ ጠየቁ። የተሰጣቸው መልስ ግን የበለጠ አሳሳቢ ነበር።

" ሌላ ቡድን ነው እየጠየቀው ያለው " በማለት ሳያገናኟቸው ቀሩ።


ያ ጥሪ የቤተሰቡ ከአቶ ዳንኤል ስልክ የተደረገላቸው የመጨረሻ ጥሪ ሆነ።

የተኩስ ድምጽ፣ የተዘጉ የመኝታ ቤቶች በሮች

በጥቃቱ ወቅት በቦታው ከነበሩ እና በሕይወት ከተረፉ ሰዎች ቤተሰቦች በሰሙት መረጃ መሠረት፣ የወርቅ ልማት ፕሮጀክቱ ሠራተኞች ጠዋት ላይ በታጣቂዎች ተከበው ነበር።

" ውስጥ ያሉት እና የጥበቃ አባላት ከውጭ የገቡት ታጣቂዎች መታኮስ ጀመሩ። ታጣቂዎች እያንዳንዱን መኝታ ቤት በሮች እየከፈቱ ሰዎችን ሲፈልጉ ነበር ብለውናል። "


በዚያን ጊዜ ዳንኤል በመኝታ ክፍላቸው ውስጥ ነበሩ።

ከጥቃቱ የተረፈ ሰው ለቤተሰቡ እንደነገራቸው፣ እሱና አቶ ዳንኤል በሌሎች ጊዜያት አብረው ያመልጡ ነበር። በዚያ ቀን ግን አቶ ዳንኤል በክፍላቸው ውስጥ ቀሩ።

" ግለሰቡ 'እኔ እንደምንም ብዬ ወጣሁ። በክፍሉ ውስጥ ነው በጥይት የተመታው። ተመልሰን ስንመጣ ያገኘናቸው ክፍላቸው በር ላይ ተገድለው ነው' ብሎናል። "

ጥቃቱ ከቆመ በኋላ ያ ሰው አቶ ዳንኤልን ከወደቁበት አንስቶ ወደ ሆስፒታል እንደወሰዳቸው ቤተሰቡ ያስረዳል።

አስከሬኑን ለመለየት የተቸገሩበት ቅጽበት

አቶ ዳንኤል መገደላቸውን ከሰሙ በኋላ ቤተሰቦቻቸው አስከሬናቸውን ለመለየት ወደ አዲስ አበባ ምኒሊክ ሆስፒታል ሄዱ።
ነገር ግን ፊታቸውን በመመልከት ብቻ ለመለየት ተቸገሩ።

" ፊቱን ለመለየት ትንሽ ችግር አጋጥሞኝ ነበር። ነገር ግን ፀጉሩን፣ እግሮቹን እና ጥፍሩን ስመለከት ዳንኤል መሆኑን አወኩኝ። "


የአራት ልጆች አባት የሆኑት ዳንኤል አስከሬናቸው ወደ አዲስ አበባ ከመላኩ በፊት በገንጂ ሆስፒታል ነበር።

ከሆስፒታሉ ለቤተሰቦቻቸው የተላከው ደብዳቤ ደግሞ በደረታቸው ግራ በኩልና በጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ከተመቱ በኋላ በከባድ ደም መፍሰስ ሕይወታቸው ማለፉን ያስረዳል።

አስከሬኑን የተመለከቱት የቤተሰብ አባል ደግሞ ቁስሉን እንዲህ ይገልጻሉ፦

" ጭንቅላቱ እና ጆሮዎቹ መካከል ብዙ ጊዜ ተመትቷል። ሁለተኛው ደግሞ በደረቱ ቀኝ እና ግራ በኩል ተመትቷል። "


የአቶ ዳንኤል ቤተሰቦች ግድያው እንዴት እንደተፈጸመ ብዙ ጥያቄዎች እንዳሏቸው ይናገራሉ።

ከሁሉም በላይ የሚጠይቁት፣ ሌሎች ሰዎች በታጣቂዎቹ ተይዘው በሕይወት ሲተርፉ አቶ ዳንኤል ለምን እዚያው ቦታ ላይ ተገደሉ ? የሚለውን ነው።

ነገር ግን አስከሬናቸውን ያዩ የቤተሰብ አባል ሞታቸው በአጋጣሚ የተፈጸመ አልነበረም የሚል እምነት አላቸው።

"በአጋጣሚ አልነበረም... ሆን ተብሎ የተደረገ ነው።"


ሌላኛው የቤተሰብ አባል ደግሞ ዳንኤልን ለቤተሰባቸው ያላቸውን ሚና ሲገልጹ፣
"አባታችን አባትም እናትም ነው። ለእኛ የእናት ልብ ያለው።"


በማለት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጠንክረው ይሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።

ሌላኛው የቤተሰብ አባል ደግሞ ዳንኤልን እንዲህ ይገልጿቸዋል፦
"እሱ ሰላማዊ ሰው ነው፣ ልጆቹን ለማሳደግ የሚሮጥ እና የሚታትር ሰው ነው። እውነቱ መታወቅ አለበት።"


ከጥቃቱ በኋላ የተዘጋው የወርቅ ማዕድን ሥራ

የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት በጥቃቱ የተከሰተውን ሞት ተከትሎ ሥራውን ማቆሙን አስታውቋል።

ኩባንያው ባወጣው መግለጫ አንድ ሠራተኛውን ጨምሮ " በርካታ [ሰዎች] ተገድለዋል " ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላትና የጸጥታ አካላት መገደላቸውን ገልጿል፣ ነገር ግን ቁጥራቸውን አላሳወቀም።

ኩባንያው የጥቃቱን ፈጻሚዎች ማንነትም በመግለጫው አልጠቀሰም።

የወረዳው አንድ ባለሥልጣን ግን ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው፣ ጥቃቱን መንግሥት "ሸኔ" በሚል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች እንደፈጸሙት ጠቁመዋል።

ከጥቃቱ አንድ ሳምንት በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በክልሉ የማዕድን ቁፋሮና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ የተሰማሩ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ማስጠንቀቁን አስታውቋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘውን የቱሉ ካፒ ፕሮጀክት ላይ የተወሰደውን እርምጃም በምሳሌነት ጠቅሷል።

የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ ለቢቢሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልጸው፣ ኮሚቴ ተቋቁሞ መግለጫ ሊሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የቢቢሲ አማርኛ ነው።

መስከረም 8 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች