ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

የጓሮ " ሌብነቶች " እና ማስፈራራቶች

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
የጓሮ " ሌብነቶች " እና ማስፈራራቶች
የጓሮ " ሌብነቶች " እና ማስፈራራቶች

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በግብር ተቆጣጣሪዎቹና በግብር ከፋዮች መካከል የሚደረጉ ሕገወጥ አሠራሮችን፣ ምዝበራንና የሙስና ቅሬታዎችን ለመግታት በሚል በቅርቡ አዲስ የቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱ ይታወሳል፡፡

በተቆጣጣሪዎች ደረት ላይ የሚገጠመውና ድምፅ እንዲሁም ምሥል በቀጥታ (Live Stream) ወደ ማዕከል የሚያስተላልፈው " የሰወነት ላይ ካሜራ " (Body-Worn Camera) ከተተገበረ ወዲህ የግብር ሰብሳቢነት አቅም ማደጉና ቅሬታዎች መቀነሳቸው ተነግሯል፡፡

ነገር ግን በተዘረጋው የቴክኖሎጂ መረብ ውስጥ ሳይያያዙ የሚያመልጡና ነጋዴውን ምሬት ውስጥ የከተቱ አዳዲስ " የጓሮ " ሌብነቶችና የማስፈራራት ሥልቶች መበራከታቸውን የሚጠቁሙ ቅሬታዎች መኖራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

ከካሜራ ጀርባ የሚደረግ የማስፈራራት እና የደላላ ሴራ

በቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች የሚሸጡ አንድ ነጋዴ የደረሰባቸውን በደል ሲናገሩ " ተቆጣጣሪዎቹ ካሜራ ያለው ዩኒፎርም ለብሰው መጥተው 'ያለደረሰኝ ሸጠሃል" አሉኝ፡፡ አልሸጥኩም ብዬ ስሞግታቸው ፈጽሞ የማላውቀውን ሰው እንደ ምስክር ይዘው መጡ፡፡ ነገሩ ወደ ሕግ እንዲሄድ ሱቅ ዘግቼ ስወጣ፣ መስካሪ የተባለው ሰው ነጠል አድርጎ ወስዶኝ 'ገንዘብ ሰጥተህ ብትገላገል ይሻላል፣ እኔ ምስክርነቴን ከተናገርኩ ደግሞ እስር ቤት ነው የምትገባው" ሲል አስፈራራኝ " ብለዋል፡፡

ነጋዴው አያይዘውም " ካሜራው በምሥልና በድምፅ ይቀርፃል መባሉ እወነት አይመስለኝም፡፡ አልያም ደግሞ ካሜራው አጠገብ ሆነው በድፍረት የኮንትሮ ባንድ ወንጀለኛ አድርገው ሲያሸማቅቁኝ ካሜራው አይሠራም ማለት ነው " ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ የመለስተኛ ሬስቶራንት ባለቤት የሆኑ አንዲት ነጋዴ ደግሞ ተቆጣጣሪዎች ቴክኖሎጂውን እንዴት እንደሚያታልሉት ያስረዳሉ፡፡

" ካሜራው የተገጠመበትን ዩኒፎርም ለብሰው መጥተው ቁጥጥር ያደርጋሉ። ከዚያም 'ምሳ አዘጋጂልን እንመለሳለን' ብለው ይወጣሉ፡፡ ሲመለሱ ግን ዩኒፎርማቸውን አውልቀውና ካሜራውን አጥፍተው ነው፡፡ የፈለጉትን ያህል በልተውና ጠጥተው፣ ሌሎችንም ጋብዘው ሳይከፍሉ ይሄዳሉ፡፡ ይህ በተደጋጋሚ የሚደረግ በመሆኑ ሠርተን የምንከፍለው ለእነሱ ሆኗል " ሲሉ ተናግረዋል።

በካራሎ አካባቢ በሚገኙ የሥጋ ቤቶችና ምግብ ቤቶች መረጃ መሠረት ደግሞ ተቆጣጣሪዎች አስቀድመው ያለ ዩኒፎርም እንደ ተራ ደንበኛ በመሆን ይመጣሉ፡፡ የፈለጉትን ከተመገቡ በኋላ ክፍያ ፈጽመው ይወጣሉ፣ ወይም ደረሰኝ ሳይቀበሉ ይሄዳሉ፡፡

ከዚያም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዩኒፎርማቸውን ለብሰውና ካሜራቸውን አብረው በመመለስ " ቅድም ያለደረሰኝ አስተናግዳችሁናል፣ እጅ ከፍንጅ ይዘናችኋል " በሚል ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያስፈራሩና ድራማዊ በሆነ መንገድ ጉቦ እንደሚጠይቁ ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በካራሎ የሚገኙ የሥጋ ቤት ባለቤቶች የግብር ከፋዮች ተቆጣጣሪዎች ያለ ክፍያ እንደሚመገቡና የታወቁ ነጋዴዎችን ስም እየጠሩ " እገሌንም ቢሆን ማንም አላዳነውም፣ ብትስማሙ ይሻላችኋል " በሚል ማስፈራሪያ፣ ገንዘብና ነፃ አገልግሎት እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።

ወደ ማዕከል የማይደርሱት ቅሬታዎች

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ኃላፊ አቶ ሰውነት አየለ፣ የካሜራ ቴክኖሎጂው በኅዳር ወር 2018 ዓ.ም. በይፋ ሥራ ከጀመረ ወዲህ በይፋ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በከፍተኛ መጠን ቀንሰዋል፣ የግብር ገቢም አድጓል፡፡

" ቴክኖሎጂው በተቆጣጣሪውና በግብር ከፋዩ መካከል የሚደረገውን የቃላት ልውውጥ በምሥልና በድምፅ በቅፅበት ወደ ማዕከል የሚያስተላልፍ ከመሆኑም በላይ፣ ጂፒኤስ (GPS) የተገጠመለት በመሆኑ ተቆጣጣሪው የት እንደሚገኝ በግልጽ ያሳያል " ሲሉ አቶ ሰወነት ያስረዳሉ።

አክለውም " ቀደም ሲል ይቀርቡ የነበሩት 'ያላግባብ ተቀጣን' ወይም 'ጉቦ ተጠየቅን' የሚሉ አቤቱታዎች አሁን ላይእምብዛም አሉ ማለት አይቻልም " ብለዋል፡፡

" ካሜራው 24 ሰዓት ሙሉ የሚቀርፅ በመሆኑ ቅሬታ የቀረበበት አጋጣሚ ሲኖር ማዕከል ላይ ተቀምጠው የሚከታተሉ ባለሙያዎች ቪዲዮውን በመመልከት ውሳኔ ይሰጣሉ " ውጤታማነቱን አብራርተዋል፡፡

ኃላፊው ቴክኖሎጂው ስኬታማ መሆኑን ቢገልጹም፣ ሪፖርተር ጋዜጣ በተለያዩ የከተማዋ የንግድ አካባቢዎችና ማዕከላት አደረኩት ባለው ቅኝት ግን የካሜራውን መኖር ተገንዝበው አሠራራቸውን የለወጡ፣ ነገር ግን ሕገወጥ ድርጊታቸውን ያላቆሙ ተቆጣጣሪዎች መኖራቸውን ያሳያል፡፡

አቶ ሰውነት ቅሬታ ያላቸው ግብር ከፋዮች በተቆጣጣሪዎቹ ዩኒፎርም ላይ ያለውን መለያ ኮድ (ID Code) በመያዝ በነፃ ስልክ መስመር 7075 ደውለው ማመልከት እንደሚችሉና ቪዲዮው ተፈትሾ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ገልጻዋል።

ነጋዴዎች ግን አቤቱታ ለማቅረብ ወደኋላ የሚሉባቸው የራሳቸው ምክንያቶች እንዳሏቸው ይናገራሉ፡፡

ነጋዴዎች " ቅሬታ ብናቀርብ አቤቱታችን ተሰሚነት አያገኝም፣ ይልቁንም ተቆጣጣሪዎቹ በግላቸው ተናደውብን የባሰ ተደጋጋሚ ቅጣትና እንግልት ያመጡብናል " የሚል ሥጋት አለባቸው፡፡

በርካታ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን የትና እንዴት ማቅረብ እንዳለባቸው፣ ወይም የ'7075' ነፃ ስልክ መስመር መኖሩን እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ለጉቦና ላልተገባ አሠራር እጅ መስጠት በሕግ ፊት ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው የሚያውቁት ነጋዴዎች፣ ጉዳዩን ወደ ሕግ ከመውሰድ ይልቅ የንግድ ጊዜያቸውን ላለማጥፋት ሲሉ አላስፈለጊውን እንግልት በዝምታ ለማለፍ ይገደዳሉ፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሰወነት ላይ ካሜራ (Body Camera) ቴክኖሎጂን መተግበሩ በግብር አሰባሰብ ሒደት ላይ ግልጽነትን ለመፍጠርና ቀጥተኛ ሌብነትን ለመቀነስ ትልቅ ዕርምጃ መሆኑ አይካድም፡፡

ነገር ግን የቴክኖሎጂው መኖር ብቻውን ሙስናን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋው አልቻለም። ተቆጣጣሪዎች ካሜራው የማይደርስባቸውን ዘዴዎች (ዩኒፎርም ማውለቅና ምስክር በማስፈራራት መጠቀም) በመጠቀም አዳዲስ የሕገወጥነት መንገዶችን መቀየሳቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ አመልክቷል።

ቢሮው የቴክኖሎጂ ቁጥጥሩን ብቻ ሳይሆን፣ ከካሜራ ውጪ የሚደረጉ የቅድመ ስለላና ድኅረ ቁጥጥር እንቅስቃሴዎችን የሚያጠኑ ድብቅ የክትትል ቡድኖችን ማሰማራት፣ ለነጋዴው የጥቆማ መስመሮች አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትና መስጠትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል።

ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የሪፖርተር ጋዜጣ ነው።

ጳጉሜን 1 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች