ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

ዲጂታላይዜሽን እና በዓላት

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
ዲጂታላይዜሽን እና በዓላት
ዲጂታላይዜሽን እና በዓላት

በቴክኖሎጂና በዲጂታላይዜሽን መስፋፋት ምክንያት ቀደም ሲል በበዓላት ወቅት በአካል ይደረጉ የነበሩ ጉብኝቶችና ሰላምታዎች እየቀነሱ መምጣታቸው በትውልዶች መካከል ያለውን የባህል፣ የታሪክና የልምድ ልውውጥ እያዳከመ መሆኑን የሶሺዮሎጂ ተመራማሪዎች ለቲክቫግ ኢትዮጵያ ገለጹ።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ መምህርና ተመራማሪ ሰመረ በየነ፣ ቀደም ሲል በበዓላት ወቅት ቤቶች በሰዎች ይሞሉ፣ ከሩቅ የሚኖሩ ወገኖች ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመጡ፣ አዛውንቶችንም በአካል ይጎበኙ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ግን በስልክ ጽሁፍ፣ በምስልና በቪዲዮ የሚላኩ የበዓል ሰላምታዎች የአካል ጉብኝትን በመተካት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ይህም የማህበረሰቡን ባህላዊ ትስስር እያላላ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ሰመረ ገለጻ፣ በአካል መገናኘት ሰላምታ ከመለዋወጥ በላይ ሰዎች ምግብና ጊዜ በጋራ በማሳለፍ የስሜትና የአብሮነት ትስስር እንዲጠናከር ያደርጋል። ይህ በትውልዶች መካከል ታሪክ፣ ባህልና ልምድ የሚተላለፍበት አንዱ መንገድም ነው።

በአንጻሩ፣ የዲጂታል ሰላምታዎች በአካል የሚደረግን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ሊተኩ እንደማይችሉ ገልጸው፣ ይህ በተለይ አዛውንት ወላጆችና ዘመዶች ላይ የብቸኝነትና የመገለል ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የቴክኖሎጂ እድል ያላገኙ ወይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችና በቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ያልተስፋፋባቸው ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ከዚህ አዲስ የግንኙነት ልማድ ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አሸናፊ ከበዴ በበኩላቸው፣ ስማርት ስልኮችና ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሩቅ ያሉ ቤተሰቦችንና ወዳጆችን በቀላሉና በዝቅተኛ ወጪ ለማገናኘት ጠቃሚ ቢሆኑም፣ በአካል የመጠያየቅን ባህል እያሳነሱ መምጣታቸው የማህበራዊ ትስስርን ሊያዳክም እንደሚችል ገልጸዋል።

በኢትዮጵያዊ ባህል እጅ ለእጅ መጨባበጥ፣ መተቃቀፍ፣ አብሮ ማዕድ መጋራትና በበዓል ወቅት ረጅም ጊዜ በአንድ ቦታ ማሳለፍ ጠንካራ የማህበራዊ ትስስር መሳሪያዎች መሆናቸውን ዶ/ር አሸናፊ ገልጸዋል።

በተለይም ከልጆቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጉብኝት የሚጠብቁ ወላጆች በስልክ ወይም በቪዲዮ የሚላክላቸው ሰላምታ የአካል ጉብኝትን ያህል ስሜታዊ እርካታ ላይሰጣቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።

ተመራማሪዎቹ በበዓላት ወቅት ወጣቶች ወደ አያቶቻቸው፣ ወላጆቻቸውና ዘመዶቻቸው በመሄድ በአካል መጠያየትን እንዲያጠናክሩ መክረዋል።
ቴክኖሎጂው የቤተሰብና የማህበረሰብ ትስስርን ለማገዝ እንጂ የአካል ግንኙነትን ለመተካት እንዳይውልም አሳስበዋል።

በተጨማሪም ሀገር በቀል እሴቶችን ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያጣጥም ሀገር አቀፍ ፖሊሲ እንዲዘጋጅ፣ ቤተሰቦችም ልጆችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶቻቸውን እንዲያውቁና እንዲጠብቁ እንዲያስተምሯቸው ጥሪ ቀርቧል።

ሁለቱም ተመራማሪዎች ዋናው ጉዳይ ቴክኖሎጂን መቃወም ሳይሆን፣ ዲጂታል ግንኙነትን ከኢትዮጵያዊ የአብሮነት ባህል ጋር በማመጣጠን በአካል የመጠያየቅ፣ የመተሳሰብና የመተባበር እሴቶችን ማስቀጠል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጳጉሜን 2 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች