ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" በገዛ ባለቤቱ ፊት ሟችን በስለት ወግተው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል "  - ኢንስፔክተር ደሳለኝ ደንጊሶ

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" በገዛ ባለቤቱ ፊት ሟችን በስለት ወግተው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል "  - ኢንስፔክተር ደሳለኝ ደንጊሶ
" በገዛ ባለቤቱ ፊት ሟችን በስለት ወግተው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል "  - ኢንስፔክተር ደሳለኝ ደንጊሶ

በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ግርማ ዋሸ ትናንት መስከረም 9 ቀን 2019 ዓ.ም. ከምሽቱ 5፡40 ገደማ ከባለቤታቸው ጋር ከሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ህመምተኛ ጠይቀው ወደ ቤታቸው እየሄዱ በስለት ተወግተው ህይወታቸው አልፏል።

የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምክትል መምሪያ አዛዥና የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ምርመራ ኃላፊ ኢንስፔክተር ደሳለኝ ደንጊሶ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደገለጹት፣ ግድያው የተፈጸመው በከተማው ቱላ ክፍለ ከተማ ቱሎ ቀበሌ አማ ፓርክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

" ተጠርጣሪዎቹ ለዝርፊያ በሚመስል መልኩ ሟች አቶ ግርማና ባለቤታቸው በእግር እየተጓዙ ባሉበት ጥቃት ፈጽመው፣ ግለሰቡን ሶስት ጊዜ በስለት እንደወጉት ባለቤቱ ባሰማችው ጩኸት አካባቢውን ለቀው ሸሽተዋል " ሲሉ አስረድተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችና ፖሊስ ደርሰው የሟችን ሕይወት ለመታደግ ቢሞክሩም አለመሳካቱን ገልጸው፣ ባለቤቱን ማትረፍ መቻሉን ኢንስፔክተር ደሳለኝ ደንጊሶ አስታውቀዋል።

" በገዛ ባለቤቱ ፊት ነው ሟችን በስለት ወግተው የተሰወሩት " ያሉት ኢንስፔክተር ደሳለኝ ደንጊሶ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ባደረገው ጠንካራ ክትትልና አሰሳ ወንጀሉን ፈጽመው ለመሰወር የሞከሩ ሶስት ተጠርጣሪዎችን በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከተደበቁበት በቁጥጥር ስር ማዋሉንም አስረድተዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች አንዱ ከዚህ ቀደምም በመሰል የዝርፊያ ወንጀል እንደሚጠረጠር ያነሱት ኢንስፔክተር ደሳለኝ፣ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን፣ የምርመራው ውጤት ሲጠናቀቅ ለአጠቃላይ ለህዝቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች