ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

" አሁን ላይ ለሚዲያ እና ለሕዝብ ለመናገር የማይመቹ አንዳንድ ከባድ ነገሮች አሉ " - ፖሊስ

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
" አሁን ላይ ለሚዲያ እና ለሕዝብ ለመናገር የማይመቹ አንዳንድ ከባድ ነገሮች አሉ " - ፖሊስ
" አሁን ላይ ለሚዲያ እና ለሕዝብ ለመናገር የማይመቹ አንዳንድ ከባድ ነገሮች አሉ " - ፖሊስ

👉 " በሟች ላይ የተፈፀመው ድርጊት እጅግ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ እና ጭካኔ የተሞላበት ነው ! "

🖇️ " በግድያው ተጠርጥረው ከተያዙት ውስጥ የሩት የቀድሞ ጓደኛ እና ፍቅረኛ ይገኙበታል "

ሰሞኑን፣ ኢትዮጵያን ወክላ በአውሮፓውያኑ 2026 'ሚስ ወርልድ' የቁንጅና ውድድር ላይ የምትሳተፈው ሩት ይርጋለም ታላቅ እህት የሆነችው ቅዱሳን ይርጋለም ታግታ ተገድላለች።

ከዚህ ግድያ ጋር በተያያዘ የሩት የቀደሞ ቅርብ ጓደኛን ጨምሮ 10 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

በግድያው የተጠረጠሩት የሩት የቀድሞ ጓደኛ እና ፍቅረኛዋ ከሌሎች 8 ተጠርጣሪዎች ጋር በመቀናጀት ሟችን " ጭካኔ በተሞላበት መልኩ በመግደል " እንደተጠረጠሩ ፖሊስ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ቶማስ እሸቴ፤ ተጠርጣሪዎቹ ግድያውን የፈፀሙት " ገንዘብ ለመቀበል በማሰብ " መሆኑን በሰጡት ቃል እንዳመኑ አስረድተዋል።

" የገንዘብ ችግር አለብን፤ ያንን የገንዘብ ችግር ለማቃለል ይህንን ወንጀል ፈፅመናል " በማለት ተጠርጣሪዎቹ ለፖሊስ በሰጡት ቃል ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ታጋቿን ለማስለቀቅ ከቤተሰቦቿ 2.5 ሚሊዮን ብር ጠይቀው እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

ገንዘቡን ለመቀበል የተለያዩ ድርድሮችን ሲያደርጉ እና ገንዘቡን የሚቀበሉላቸውንም ሰዎች ሲልኩ እንደነበርም ተገልጿል።

ዕድሜዋ 30 የነበረው ሟች ቅዱሳን ይርጋለም የልብስ ዲዛይነር ስትሆን፤ በተጓዳኝም የተለያዩ የጌጣጌጥ ሥራዎችን ትሸጥ ነበር።

ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በሰጡት ቃል እንዳመኑ የተናገሩት ኮማንደር ቶማስ፤ ወንጀሉን በየትኛው ቦታ እና በምን ዓይነት መንገድ እንደፈፀሙት እማኞች ባሉበት፣ ቦታው ድረስ መርተው በመውሰድ ማሳየታቸውን አስረድተዋል።

በምርመራው ወቅት የነበረውን ሒደት እንደ እማኝ ቀርቦ ሲከታተል የነበረው የሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር አዘጋጆች ተወካይ አቶ አበባው አበበ እንዳሉት፤ በወንጀሉ ከተጠረጠሩት ሰዎች መካከል አንዷ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ የሩት የቅርብ ጓደኛ የነበረች ናት።

ሩት ከተጠርጣሪዋ ጋር በጊዜ ሒደት ጓደኝነታቸው እየጠበቀ በመምጣቱ፤ እንደ ቤተሰብ በመቀራረብ ጭምር ይተዋወቁ እና ይጠያየቁም እንደነበር ያብራራሉ።

ነገር ግን ከባለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በመካከላቸው በተፈጠሩ የተለያዩ አለመግባባቶች ምክንያት ግንኙነታቸውን አቋርጠው እና ተራርቀው እንደነበር ተናግረዋል።

አርብ ሐምሌ 10/ 2018 ዓ. ም. የሩት የቀድሞ ጓደኛ ማንነቷን ደብቃ እና በሌላ ሰው ስም በመጠቀም ለቅዱሳን ደውላለች።

ደዋይዋ ሁለት ወር ያለፈውን የሩትን ልደት " ሰርፕራይዝ ለማድረግ " እንዳሰበች እና ሟች የምትሸጣቸውን ጌጣጌጦች መግዛት እንደምትፈልግ ገልጻ ቀጠረቻት።

ቅዱሳንም ጉዳዩን በማመን አርብ ረፋድ አካባቢ ሜክሲኮ በሚገኝ ጭማቂ ቤት የተገኘች ሲሆን፤ በቦታው ስትደርስ ግን የቀጠራት ሰው በሌላ ስም የደወለችው የእህቷ የቀድሞ ጓደኛ ናት።

አቶ አበባው እንዳሉት፤ ተጠርጣሪዋ " ከዚህ ቀደም አስቀይሜያችሁ ስለነበር እውነቴን ብነግርሽ አትመጪልኝም ብዬ በማሰብ ነው በሌላ ሰው ስም የደወልኩልሽ " ብላታለች።

ሟች ቅዱሳን በበኩሏ ለተጠርጣሪዋ ምላሽ ስትሰጥ " እኛ ብንቀየምሽ ኖሮ እኮ እናትሽ ታማ በነበረበት ወቅትም ሆነ ስታርፍ መጥተን አንጠይቅሽም ነበር፤ ስለዚህ እኛ ምንም አልተቀየምንም " በማለት እንደመለሰችላት አስረድተዋል።

በመቀጠል ተጠርጣሪዋ " አዲስ ቤት ተከራይቻለሁ፤ ስለዚህ መጥተሽ ቤቴን ብታይልኝ ደስ ይለኛል " ስትል ቅዱሳንን እንደጠየቀቻት እና አክላም " አሁን ላይ ሕይወቴ በጥሩ ሁኔታ ተሻሽሎልኛል፤ በዚያ ላይ ለአንቺም የምትሠሪያቸውን ሥራዎች ይዤ ስለመጣሁ እዚያው ቤቴ ሆነን እናወራለን " በማለት ኮዬ ፈጬ አካባቢ ወደ ተከራየችው ኮንዶሚኒየም ቤቷ ወስዳታለች።

በአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ መሠረት፤ ተጠርጣሪዎቹ ቅዱሳንን ካገቱበት ኮዬ ፈጬ ከሚገኘው ኮንዶሚኒየም ሌላ ቤት በመከራየት አዘዋውረዋል።

ቅዱሳን ከታገተችበት አርብ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሞተች እስከታመነበት እሑድ ሐምሌ 12/ 2018 ዓ. ም. ድረስ "ምግብ እንዳልሰጧትም" ተነግሯል።

ተጠርጣሪዎቹ ቅዱሳን ላይ ግድያ ከፈፀሙባት በኋላ ለቤተሰቦቿ ደውለው ገንዘብ መጠየቃቸውን የምርመራ ሒደቱ ማሳየቱን ኮማንደር ቶማስ ገልጸዋል።

ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ አበባው፤ ግድያው እሑድ ዕለት የተፈፀመ ሲሆን፤ አጋቾቹ ግን ሰኞ ዕለት እሷን በሕይወት ለማስለቀቅ በሚል ከቤተሰቧ ገንዘብ መጠየቃቸውን ቀጥለው ነበር።

የሩት የቀድሞ ጓደኛ እና ፍቅረኛዋ ቅዱሳንን "በግፍ ለመግደል" የወሰኑበት ዋና ምክንያት "ካየችሽ ስለምታውቅሽ ልታስይዘን ትችላለች" ብለው በመስጋት እንደሆነ ያስረዳሉ።

የግድያ ሁኔታውን አስመልከቶ የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ኮማንደር ቶማስ " አሁን ላይ ለሚዲያ እና ለሕዝብ ለመናገር የማይመቹ አንዳንድ ከባድ ነገሮች አሉ " በማለት ዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

" በሟች ላይ የተፈፀመው ድርጊት እጅግ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ እና ጭካኔ የተሞላበት ነው " ሲሉ ወንጀሉ ምን ያህል ዘግናኝ እንደነበርም ገልጸዋል።

ይህንን አሰቃቂ ድርጊት በቀጥታ ፈፅመዋል ተብለው ከተጠረጠሩት የሩት የቀድሞ የቅርብ ጓደኛ እና ፍቅረኛዋ በተጨማሪ፤ ከጉዳዩ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 8 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ፖሊስ አሳውቋል።

ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የቢቢሲ አማርኛ ነው።

ሃምሌ 23 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች