ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#እንድታውቁት

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#እንድታውቁት
#እንድታውቁት

በየዓመቱ የበጀት ዓመቱ ሲጠናቀቅ የዳኝነት አገልግሎት ክብደትና ውስብስብነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የፌዴራል የመጀመሪያ፣ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 ለ2 ወራት በከፊል ዝግ ሆነው የሚቆዩ መሆኑ ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዝግ ሆኖ በሚቆይበት የክረምት ወራት በተረኛ ችሎት የሚያስተናግዳቸውን አስቸኳይ ጉዳዮች አሳውቋል።

ፍርድ ቤቱ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳመለከተው፣ አገልግሎቱ የሚሰጠው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ 3 በተደነገገው መሠረት ነው።

ይህም መሰረታዊ የመብት ጥሰት እንዳይከሰት እና አፋጣኝ ውሳኔ ካልተሰጠባቸው ሊካስ የማይችል ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮችን ለመፍታት የታለመ እንደሆነ ተገልጿል።

በዚሁ መሠረት በክረምቱ የተረኛ ችሎት የሚታዩ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዝርዝር፦

• አስቸኳይ የእግድ አቤቱታዎች እና የልጅ ቀለብ ጥያቄዎች፣
• አካል ነጻ ለማውጣት እና እንቅስቃሴን ገዳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚቀረቡ አቤቱታዎች፣
• የሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ አፈጻጸም ጉዳዮች፣
• ከግልግል ዳኝነት ትዕዛዞች ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ አስቸኳይ የማኅተም አገልግሎት ጥያቄዎች፣
• እንዲሁም ሌሎች መደበኛ የሥራ ጊዜን መጠበቅ የማይችሉ አጣዳፊ ጉዳዮች በዳኛው ውሳኔ የሚስተናገዱ ይሆናል።

በወንጀል ጉዳዮች በኩል ደግሞ የሚከተሉት ነጥቦች ተለይተዋል፦

• የዋስትና እና የአምክሮ ጥያቄዎች፣
• እስረኛ ያለባቸው የክስ መዛግብት፣
• የጊዜ ቀጠሮ ጉዳዮች (በአራዳ ምድብ ችሎት)፣
• በተሰብሮ የሚቀርቡ አቤቱታዎች እና ለመሰየም የሚቀርቡ ጥያቄዎች፣
• ሌሎች ጊዜ የማይሰጡ አንገብጋቢ የወንጀል ጉዳዮች ይስተናገዳሉ።

ፍርድ ቤቱ በከፊል ዝግ በሆነባቸው በእነዚህ ሁለት ወራት፣ ለዳኞች ተራ ወጥቶ አገልግሎቱ እንደሚሰጥ የገለጸ ሲሆን፤ የፍርድ ቤቱ ማኅበረሰብም ሆነ ተገልጋዩ ለሥራው መሳካት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች