ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

የብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም ወደ መንግሥት ልማት ድርጅትነት መሸጋገሩን ይፋ አደረገ።

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

·

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
የብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም ወደ መንግሥት ልማት ድርጅትነት መሸጋገሩን ይፋ አደረገ።
የብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም ወደ መንግሥት ልማት ድርጅትነት መሸጋገሩን ይፋ አደረገ።

ዜጎች አስፈላጊ ዶክመንቶቻቸውን የሚያስቀምጡበት ዲጂታል ዋሌትና የፊት ገጽ ማረጋገጫ ሥርዓት ይፋ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም ከአምስት ዓመታት የትግበራ ሂደት በኋላ “ፋይዳቨርስ” (FaydaVerse DPI Solutions) በተሰኘ ስያሜ አዲስ የዲጂታል ህዝባዊ መሠረተ-ልማት (DPI) አልሚ ተቋም በመሆን ወደ መንግሥት ልማት ድርጅትነት መሸጋገሩን በይፋ አብስሯል።

ቀደም ሲል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር ተቋቁሞ ሲሠራ የቆየው ይህ ፕሮግራም፣ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) ሥር በመጠቃለል ተቋማዊ ሽግግር ማድረጉን ገልጿል።

በዛሬው ዕለት በተከናወነው የምስረታ መርሃ-ግብር ላይ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ብሩክ ታዬን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና የዘርፉ ተዋናዮች ታድመዋል።

በዕለቱ የፋይዳቨርስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮዳሔ አርአያሥላሴ ተቋሙ የስም ለውጥ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ የቴክኖሎጂ አቅሞችንና አገልግሎቶችን ይዞ መቅረቡን ለታዳሚያን ገልጸዋል።

በዚህም የደንበኞችን ማንነት በዲጂታል መንገድ የማረጋገጥ ሥርዓትን (eKYC) ከኦቲፒ (OTP - One-Time Password) በተጨማሪ የፊት ገጽታን (Face ID) እና የባዮሜትሪክስ ማረጋገጫ ሥርዓቶችን ያካተተ አገልግሎት መጀመሩን አብስረዋል።

በተጨማሪም "ፋይዳ ፓስ" የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ማልማቱንና ዜጎች አስፈላጊ ሰነዶቻቸውን (የመታወቂያ፣ የትምህርትና ሌሎች ምስክር ወረቀቶችን) በአንድ የዲጂታል ዋሌት የሚያገኙበትን አማራጭ ያካተተ ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

አቶ ዮዳሔ አክለውም፤ ፋይዳቨርስ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በመሠረተ-ልማት ግንባታ፣ በማማከርና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ተቋም ለመሆን እቅድ ማሰቀመጡን አስረድተዋል።

በዚህም እስካሁን ከሞዛምቢክ፣ ከዛምቢያ፣ ከብሩንዲ እና ከኒጀር ጋር በቴክኒክ ድጋፍ፣ በመሠረተ-ልማት ግንባታ፣ በሥርዓት ማቀናጀትና በሰራተኞች ሥልጠና ዙሪያ የጋራ አጋርነት ስምምነቶች መከናወናቸው ገልጸዋል።

የብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም እስካሁን ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መመዝገብ የቻለ ሲሆን፣ እስከ 2026 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የተመዝጋቢዎችን ቁጥር 90 ሚሊዮን ለማድረስ አቅዷል።

እስካሁን ባለው ሂደት 190 ሚሊዮን የኢ-ኬዋይሲ (eKYC) የማረጋገጫ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በቀን ከ2 ሚሊዮን በላይ የማረጋገጫ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተጠቅሷል።

ባንኮችን፣ የክፍያ ተቋማትን እና የቴክኖሎጂ ስታርት-አፖችን (አዲስ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን) ጨምሮ 165 ተቋማት ከሥርዓቱ ጋር ትስስር ሲፈጥሩ፤ ከ12,000 በላይ የመመዝገቢያ ማሽኖች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። እስካሁንም ከ15 ሚሊዮን በላይ የፋይዳ ካርዶች ታትመው ተሰራጭተዋል።

ይህ የዲጂታል ማንነት መሠረተ-ልማት እስከ 2030 ድረስ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርትን (GDP - Gross Domestic Product) በ6 በመቶ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ሃምሌ 28. ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች