ወደ ይዘቱ ዝለል
ቀጥታ ዝማኔ
ሀሁኒውስ

ግልጽና የታመነ ዜና

#NationalDialogue🇪🇹

ምንጭ፦ TIKVAH Ethiopia

¡

አጋራXFacebookTelegramLinkedIn
#NationalDialogue🇪🇹
#NationalDialogue🇪🇹

የመንግስት አደረጃጀት እና ቅርፅ ምክክር

በሀገራዊ ምክክሩ የመንግስት አደረጃጀት እና ቅርፅ በተሰኘው አጀንዳ ላይ ተሳታፊዎች ባደረጉት ምክክር የፌደራል አወቃቀር ፌዴራሊዝም ሆኖ እንዲቀጥል አመዛኝ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን፣ በመንግስት አደረጃጀት ደግሞ የጠቅላይ ሚነስትሩና የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ጉዳይ በአመዛኙ አከራካሪ ሀሳቦች እንደቀረቡበት ተገለጸ።

በ10 እና 50 ሰዎች የተደራጁ ንዑሳንና ጥቃቅን ቡድኖች በስምንቱም አጀንዳዎች ተወያይተው ካነሷቸው ሀሳቦች ውስጥ 250 ሰዎችን ለያዘው ቡድን ሲቀርቡ ያልተካተቱት እንዲካተቱ የሚያደረግበትና 250ዎቹ ምክረ ሀሳቦቹን የሚያጠናክሩበት ውይይት ትላንትም ቀጥሎ ተካሂዷል።

ይሄው ተግባር ከተከናወነባቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱ የሆነው የመንግስት አደረጃጀትና ቅርፅ የተሰኘው አጀንዳ ሲሆን፣ 250 ሰዎችን በያዘው ቡድን ምን ሀሳቦች እንደተነሱ ማብራሪያ ጠይቀናል።

በዚሁ አጀንዳ፥ 10፣ 50፣ 250 በያዙ ሰዎች የተደራጁ ቡድኖችን ሀሳብ በማጠናቀር፣ በፀሐፊነትና በሰብሳቢነት እየሰሩ ያሉት አቶ ሰለሞን ገብሬ፣ የምክረ ሀሳቦች ጥቅምና ጉዳት ጭምር ተዝርዝሮ 250 ሰዎችን በያዘው ቡድን ምክረ ሀሳብ የማቅረቡ ጉዳይ ተጠናቆ ለቀጣዩ 500 ሰዎች የያዘ ቡድን ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።

1. የመንግስት አደረጃጀት እና የሥልጣን ክፍፍል

በመንግስት አደረጃጀትና ቅርፅ አጀንዳ፣ የመንግስት አደረጃጀት ፓርላሜንታዊ ወይም ፕሬዚዳንታዊ ይሁን ? የሚሉ አማራጭ ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የፕሬዚዳንቱ ስልጣን፣ አመራረጥ አከራካሪ ሆኗል።

በኢትዮጵያ የመንግስት አደረጃጀት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ፣ ፕሬዚዳንቱ ደግሞ ርዕሰ ብሔር ሆኖ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባሉ። ይህን ተከትሎ ተመካካሪዎች ከስልጣን ክፍፍል ጋር በተያያዘ የተለያዩ ምክረ ሀሳባቸውን አቅረበዋል።

አቶ ሰለሞን እንደገለጹት፣ " ፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ሰጭ አይደለም። እንግዳ ተቀባይና እንግዳ ሸኝ ነው። ስለዚህ ፕሬዚዳንት ቢሮ ውስጥ የሚመደበው በጀት ውሳኔ የማይሰጥበት የሚባክን ነው። ስለዚህ ሁለቱም ስልጣኖች ተጠቅልለው ፕሬዚዳንቱ ጋር ይሂዱ፤ አንድ ርዕሰ ብሔር ይኑረን " የሚል ሀሳብ ከተሳታፊዎች ቀርቧል።

በአንፃሩ ደግሞ፣ "ፕሬዚዳንቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይኑሩ፤ ስልጣን ግን ይከፋፈሉ። ሁለቱም በየራሳቸው የሚጠይቁበት የኃላፊነት ስልጣን ይከፋፈሉና ያን ስርዓት እንከተል" መባሉን ተናግረዋል።

በተያያዘ፣ "ፕሬዚዳንታዊን ከመረጥን ቀጥታ አሁን ባለው በፓርላማ በሚመረጠው መንገድ ይመረጥና የሁለቱንም ሥራ ጠቅልሎ ይያዝ፤ ጠቅላይ ሚነስትር የሚለው ቀርቶ ፕሬዚዳንት ይሁን" የሚል ምክረ ሀሳብ መንጸባረቁን ፀሐፊው ተናግረዋል።

እንዲሁም፣ "ፕሬዚዳንቱ ከህዝቡ ይመረጥ። ያለፈው ፓርቲ ፕሬዚዳንት ያቅርብ። የቀረቡት እጩዎች ህዝቡ ውስጥ ገብተው የምረጡኝ ቅስቀሳ አቅርበው ከህዝብ ተመርጠው ይቅረቡ። ተመራጩ ተጠሪነቱ ለህዝብ ይሁን" በሚል ሀሳብ መሰንዘሩም ተገልጿል።

በሌላ በኩል፣ "ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ይምጣና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ከፕሬዚዳንቱ የሚሰየም ሥራ ግን ተከፍሎ ይሰጠው" የሚል አማሪጭ ሀሳብ ቀርቧል። "ፕሬዚዳንቱ በህዝብ ይመረጥ ወይስ በፓርላማ?" የሚለውም አከራክራል።

በዚሁ አጀንዳ በ250 ሰዎች በተደራጀው ስልታዊ ቡድን እየተሳተፉ ያገኘናቸው የጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ተወካይ አቶ ሳይመን ቱት፣ የመንግስት አደረጃጀት ፓርላሜንታዊ፣ ፕሬዚዳንታዊ ወይስ ቅይጥ ይሁን ? በሚለው፣ " አብዛኛዎቹ ፓርላሜንቲዊ ቢሆን ይሻላል የሚል ሀሳብ አለ። እኛ እንደ ፓርቲ ፕሬዚዳንታዊ ነው የምንፈልገው " ብለዋል።

2. የሥልጣን ዘመን ገደብ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የፕሬዚዳንቱን የሥልጣን ዘመን ገደብ በተመለከተ እስካሁን ተሳታፊዎች ባቀረቡት ምክረ ሀሳብ፣ "በሁለት ተርም ይገደብ" የሚለው አመዛኝ መሆኑም ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ የመንግስት አደረጃጀት የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን በ6 ዓመት ሲገደብ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ግን እንዳልተገደበ የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ " ስለዚህ ፕሬዚዳንት ይሁን 6 ዓመቱን (በሁለት የምርጫ ተርም) እንዳለ እንውሰደው፤ ሁሉም ነገር በጠቅላይ ሚኒስትር የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ 5 ዓመት (በሁለት የምርጫ ተርም) ይሁን " የሚል ሀሳብ ከተወያዮች መነሳቱን ገልጸዋል።

3. የሕገ-መንግስቱ መግቢያ

አቶ ሳይመን ቱት፣" የህገመንግስታችን መግቢያ ምን ይሁን ? " በሚለው ጉዳይ ደግሞ፣ ወደ አራት አማራጮች መቅረባቸውን ገልጸው፣ " አብዛኛው የደገፈው የሕብረ ብሔር የኢትዮጵያ ህዝቦች እንዲባል " በሚለው መሆኑን ተናግረዋል።

4. የፌደራል አወቃቀር ፦ አሀዳዊ፣ ፌደሬላዊ ወይስ ኮንፌዴራላዊ?

በተሳታፊዎች የፌደራል አወቃቀርን በተመለከተ አሀዳዊ ወይስ ፌደሬላላዊ ወይስ ኮንፌዴራላዊ ይሁን ? በሚል አማራጮች ማቅረባቸውን ደግሞ አቶ ሰለሞን ገብሬ አስረድተዋል።

የስልጣን ምንጭ ከአንድ አካል በመሆኑ አሁን ካለው የብሔረሰቦች አወቃቀር አንፃር "አሀዳዊ አይጠቅመንም"፣ ኮንፌዴራሊዝምም "ውስብስብ ስለሆነ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የብሔረሰቦች አወቃቀር አንጻር ተግባራዊ ለማድረግ ገና ነን፤ ይቅርብን" በሚል "የፌዴራሊዝም" አወቃቀር እንዲኖር በአመዛኙ መመከሩን ገልጸዋል።

ፌደራሊዝም ይሁን ሲባል፦
- የብሔር ፌዴራሊዝም እንዳለ ይቀጥል፣
- የጂኦግራፊ ፌዴራሊዝም ይቀጥል፣
- የሁለቱም ቅይጥ ይሁን የሚሉ ሦስት ምክረ ሀሳቦች ጠንካራና ደካማ ጎናቸው ተዘርዝሮ፣ ደካማ ጎኖቹ የሚሻሻሉበት ሀሳብ ቀርቦ እንደ አማራጭ መቅረባቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን ትከተል የሚል አመዛኝ ሀሳብ መሰጠቱን፣ ነገር ግን አሁን ያለው የብሔር ፌዴራሊዝም በመሆኑ " ኢትዮጵያውያንን በብሔር ከፋፍሎናል፤ ይሄ ለመፈናቀል አብቅቶናል፤ አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር የሚያጠቃበትን ሁኔታ ፈጥሯል፤ አነስተኛ ቀጥር ያላቸው ብሔሮች እንዳይጎሉ ከልክሏል " የሚል ደካማ ጎን እንደተሳበት ገልጸዋል።

" የአንዱን ክልል ብሔር ንብረት ካፈራህበት ክልል 'ውጣ' እስከመባል ድረስ ያደረሰው ፌዴራሊዝሙ የብሔር ፌዴራሊዝም በመሆኑ ነው። ይሄ የሆነው የብሔር ፌዴራሊዝም ችግር ኑሮበት ሳይሆን የተገለገልንበት መንገድ ጤናማ ስላልሆነ በመሆኑ ይህ መስተካከል አለበት " በሚል ፌዴራሉዝም እንዲቀጥል ሀሳብ መቅቡን ተናግረዋል።

5. የስልጣን ክፍፍል እና አንቀጽ 39

የፌደራልና እና የክልል መንግስታት የስልጣን ክፍፍልን በተመለከተ፥ ለፌደራል መንግስት እና ለክልል መንግስታት የሚሰጡ ስልጣኖች በሕገ መንግስቱ እንዲቀመጡ፣ አሁን የሌሉ ከሀገር እድገት ጋር ለወደፊት የሚመጡ ጉዳዮች ቢኖሩ ስልጣን የፌደራል መንግስት እንዲሆን በሕገ መንግስት ይጠቀስ፣ አሁን ባለበት ለክልል መንግስታት ሆኖ ይቀጥል የሚሉ ሀሳቦች ቀርበዋል።

ሕገመንግስቱን በተመለከተ አንቀጽ 39 ላይ "መገንጠል" የሚለው ይውጣ፤ ባለበት ይቀጥል የሚሉ ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውን ተገልጿል።

ማጠቃለያ ፦

ሌሎች ተመካካሪዎች ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች የተለያዩ ሀሳቦች መነሳታቸውን ገልጸው፣ ምክረ ሀሳቦቹ ግን ውሳኔ እንዳልተሰጠባቸውና ገና ለቀጣዮቹ ቡድኖች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ

@tikvahethiopia

ተዛማጅ ታሪኮች